በክልሉ ከ3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት የተጀመሩ የከተማ ልማት ስራዎች እየተፋጠኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ከ3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት የተጀመሩ የከተማ ልማት ስራዎች እየተፋጠኑ ነው

አዳማ፤ ሐምሌ 2/2017(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በህዝብና በመንግሥት ትብብር ከ3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በሚበልጥ በጀት የኮሪደር እና ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑን የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ጨምር ኃይሌ ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ ከሰው ኑሮ ጋር ቀጥታ ቁርኝት ያላቸውና የዋጋ ንረትን ሊያቃልሉ የሚችሉ ፕሮጀክቶች በግንባታ ሂደት ላይ ይገኛሉ።
በዚህ ረገድ ካለፈው ታህሳስ ወር ወዲህ 165 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት በመፋጠን ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
የክልል ማዕከላት በሆኑት ሆሳዕና፣ ቡታጅራ፣ ወልቅጤ፣ ዱራሜ፣ ሀላባ ቁሊቶ፣ ወራቤና ሳጃ ከተሞች እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት አፈጻጸሙ በየሳምንቱ እየተገመገመ በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት በተደረገው እንቅስቃሴ 28 ኪሎ ሜትር የሚሆን የኮረደር ልማት ስራ እየተገባደደ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ስራውን ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ ርብርብ ይደረጋል ብለዋል።
በክልሉ ከተሞች የ90 ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው የፕሮጀክቶቹ ግንባታ በ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ወጪ እየተከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ከፕሮጀክቶቹ መካከል የህዝብ መድሃኒት ቤት፣ የጤናና የትምህርት ቤት ግንባታዎች፣ የከተማ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታዎች እንደሚጠቀሱ አስረድተዋል።
እስካሁን በተደረገው ርብርብ የ48 ፕሮጀክቶች ግንባታ መጠናቀቁን ጠቅሰው የቀሪዎችም ግንባታ በመፋጠን ላይ መሆኑን አብራርተዋል።
ሁሉም የልማት ፕሮጀክቶች ሙሉ ለሙሉ ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ህዝብ ተጠቃሚ እንደሚያደርጉም አመልክተዋል።
ከእነዚህ የልማት ስራዎች በተጓዳኝ በክልሉ ሰባት ማእከላት የርእሰ መስተዳደር ጽህፈት ቤትን ጨምሮ እሰከ 8 ወለል ህንጻ ያላቸው የአስተዳደር ማዕከላት ህንጻ ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ በ29 ከተሞች የአገልግሎት አሰጣጥን በዲጂታል ዘዴ ለማስደገፍ ታቅዶ በበጀት ዓመቱ በ14 ከተሞች ተግባራዊ ማድረግ መቻሉን አስታውሰዋል።
በዚህም የመሬትና የግንባታ ፍቃድ አገልግሎት አሰጣጥ ከእጅ ንክኪ የጸዳ ሆኖ በበይነ መረብ ተገልጋዮች ባሉበት ሆነው እየተገለገሉ መሆኑንም አውስተዋል።