ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እየሆንን ነው- ኢንተርፕራይዞች

ሀዋሳ፤ ሐምሌ 2/2017 (ኢዜአ)፦ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን በሲዳማ ክልል የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች ገለጹ።

ኢንተርፕራይዞቹ በመንግስት የሚዘጋጁ አውደ ርዕይና ባዛሮች የገበያ ትስስር ለመፍጠር እያገዟቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

''የኢንተርፕራይዞች ሚና ለሃገር ብልጽግና'' በሚል መሪ ሀሳብ በሀዋሳ ከተማ እየተከሄደ ባለው አውደ ርዕይና ባዛር በግብርና፣ በኢንደስትሪና አገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ከ220 በላይ ኢንተርፕራይዞች እየተሳተፉ ነው፡፡ 

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ኢንተርፕራይዞች እንደገለጹት፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ አምርተው ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መጥተዋል።

የ"ዮናስ አርት ሜታል" መስራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮናስ ገብሩ ማህበራቸው የተለያዩ የሕክምና መገልገያ ቁሶችና የብረታብረት ሥራዎችን እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡


 

በዚህም በከፍተኛ ወጪ ከውጭ ሀገር የሚገቡና ለሕክምና አገልግሎት የሚውሉ የታማሚ፣ አስታማሚና የህጻናት አልጋና ወንበር በጥራት በማምረት በተመጣጣኝ ዋና እንደሚያቀርብ ገልጸዋል፡፡

ይህም የውጭ ምንዛሬን በማስቀረት በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ አበርክቶ አለው ያሉት አቶ ዮናስ፣ በባዛሩና በአውደ ርዕዩ መሳተፋቸው ከተለያዩ ተቋማት ጋር የገበያ ትስስር ለመፍጠር አስችሎናል ብለዋል።

ከከሉ ከተማ አስተዳደር የመጣውና የእንጨት ምርቶችን በማምረት ሥራ የተሰማራው ቱርስታርስ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት አልቢራኢ ታደለ በበኩሉ፣ ማህበሩ ከውጭ የሚገቡትን የሚተካ ምርት እንደሚያመርትና ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር መቻሉን ተናግሯል።  


 

በክልሉ መንግስት በሚዘጋጁ ባዛሮችና አውደ ርዕዮች የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንዳስቻላቸው ገልጾ፣ ማህበሩ ጥራቱን ጠብቆ  ከሚያቀርበው ምርት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱ እያደገ መሆኑን ተናግሯል። 

በ150 ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች ንብ እያረቡ ማር፣ ሰምና ንግስት ንቦችን ለገበያ እንደሚያቀርቡ የገለጹት ደግሞ ከዳራ ወረዳ በመምጣት የተሳተፉት የባካልቾ ንብ እርባታ ማህበር ሰብሳቢ አቶ ትግሉ ዮሐንስ ናቸው፡፡ 

ማህበራቸው ጥራት ያለውን ማር ለሃገር ውስጥ ገበያ እንደሚያቀርብና በቀጣይም ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ዕቅድ እንዳለው ተናግረዋል፡፡


 

የሲዳማ ክልል ሥራና ክህሎት ልማት ቢሮ ምክትልና የሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ከፍያለው ከበደ በባዛርና አውደ ርዕዩ በግብርና፣ ኢንደስትሪና አገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ 220 ኢንተርፕራይዞች መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የአሁኑን ጨምሮ ከ5 ሺህ በላይ ኢንተርፕራይዞች የተሳተፉበት ባዛርና አውደ ርዕዮች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰው፣ በዚህም ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ግብይት ተፈጽሟል ብለዋል፡፡


 

ባዛርና አውደ ርዕዩ ለኢንተርፕራይዞች ከሚፈጥረው የገበያ ትስስር በተጨማሪ ልምድ ለመለዋወጥና በሀገር ውስጥ ምርት የመጠቀም ልምድን ለማጎልበት ሚናው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በተገኙበት በሀዋሳ ሚሌኒየም አደባባይ የተከፈተው የኢንተርፕራይዞች ባዛርና አውደ ርዕይ እስከ ነገ እንደሚቆይ ለማወቅ ተችሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም