በባሌ ዞን የ247 ኪሎ ሜትር የነባር መንገድ ጥገና እና የጠጠር ማንጠፍ ስራ ተከናውኗል - ኢዜአ አማርኛ
በባሌ ዞን የ247 ኪሎ ሜትር የነባር መንገድ ጥገና እና የጠጠር ማንጠፍ ስራ ተከናውኗል

ሮቤ ፤ ሐምሌ 2/2017(ኢዜአ)፦ በባሌ ዞን በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የ247 ኪሎ ሜትር የነባር መንገድ ጥገናና የጠጠር ማንጠፍ ስራ መከናወኑን የዞኑ መንገዶችና ሎጂስቲክስ ጽህፈት ቤት ገለጸ።
የዞኑ መንገዶችና ሎጂስቲክስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዴከማ ቦኮሉ ለኢዜአ እንደገለጹት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በዞኑ የገጠር መንገድ ተደራሽነትን ይበልጥ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርቷል።
በዚሁ መሰረት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የ247 ኪሎ ሜትር የነባር መንገድ ጥገናና የጠጠር ማንጠፍ ስራ መከናወኑን አመልክተዋል።
ከመንገዶቹ መካከል 160 ኪሎ ሜትሩ የነባር መንገድ ጥገና ሲሆን ቀሪው ከዚህ በፊት የግንባታ ስራው ተጠናቆ በበጀት ዓመቱ ጠጠር የማንጠፍ ስራ የተከናወነለት መሆኑን ገልጸዋል።
ጥገና ከተደረገላቸው መንገዶች መካከል ከሐንጌቱ - ገርቢጋሎ እና ከጎባ-ሼደም መንገድ የሚጠቀሱ መሆኑን ገልጸው፤ ሆማ -ጉለንሾ ፣ ኦቦራ -ጉልቾ ደግሞ የጠጠር ማንጠፍ ስራ የተከናወነላቸው መንገዶች ናቸው ብለዋል።
የግንባታ ስራቸው በመካሄድ ላይ ካሉ አምስት ድልድዮች መካከልም የአንዱ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑን ጠቁመው የቀሪዎቹ የግንባታ ስራ ከ30 እስከ 70 በመቶ አፈጻጸም ላይ መድረሱን አስረድተዋል።
አቶ ዴከማ እንዳሉት ለመንገዶችና ድልድዮች ጥገናና የግንባታ ስራ ከ190 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግስት በጀትና የህብረተሰቡ ተሳትፎ ጥቅም ላይ ውሏል።
መንገዶቹ ወደ ሙሉ አገልግሎት እንዲገቡ መደረጉ የህዝቡን የእለት ተእለት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማሳለጥ የጎላ አስተዋፅኦ እንዳለውም አመልክተዋል።
ህብረተሰቡም በየአካባቢው የተገነቡ መንገዶች ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ተገቢውን ጥበቃ እንዲያደርግም አቶ ዴከማ ጠይቀዋል።