ብሪክስ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ለምታደርገው ጥረት እውቅና ሰጥቷል - ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/2017(ኢዜአ)፦ 17ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ለምታደርገው ጥረት እውቅና መቸሩን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

ኢትዮጵያ በብራዚል በሚካሄድው የኮፕ 30 ጉባኤ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል አጀንዳዎቿን ለማንጸባረቅ ዝግጅት እያደረገች መሆኑንም ጠቁመዋል።

17ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ በብራዚል ሪዮ ዴጄኔሮ ተካሄዷል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ በጉባኤው ላይ ተሳትፏል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ልዑኩ በጉባኤው ላይ የነበረውን ተሳትፎ አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ሚኒስትሯ ጉባኤው ዓለም ለአየር ንብረት ለውጥ በሚፈለገው መጠን ምላሽ እየሰጠ ባልሆነበት ወቅት በጉዳዩ ላይ የያዘው ጠንካራ እና ግልጽ የሆነ አቋም ለኢትዮጵያ፣ ለቀጣና እና አፍሪካ አዎንታዊ አንድምታ እንዳለው ገልጸዋል።

የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ የሆኑ ሀገራት ከልማታቸው ጎን ለጎን የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት እንዳለባቸው መግለጹን አመልክተዋል።

የዓለም ማህበረሰብ የአየር ንብረት ለውጥ ገፈት ቀማሽ ለሆኑ ሀገራት የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ መቅረቡን ተናግረዋል።

ጉባኤው ከተወያየባቸው አጀንዳዎች መካከል ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል እየወሰዷቸው ያሉ እርምጃዎች ይገኝበታል።

ሚኒስትሯ በማብራሪያቸው ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ እያከናወነች የምትገኘው የደን ጥበቃ እና የደን መልሶ ማልማት ስራዎች፣ የኢነርጂ እና የግብርና ስራዎች እውቅና መስጠቱን ገልጸዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስራዎች የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያደርግ መጠየቁን ነው ያነሱት።

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ለምታደርገው ጥረት በብሪክስ ያገኘችው እውቅና ትልቅ አንድምታ እንዳለው ገልጸዋል።

ብሪክስ የተደረሰበት ስምምነት እንደ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂ የሆኑ ሀገራት አማራጭ ፋይናንስ ለማግኘት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር አመልክተዋል።

30ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 30) በህዳር ወር 2018 ዓ.ም በብራዚል ቤለም ከተማ ይካሄዳል።

ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በሪዮ ዴጄኔሮ አየር ንብረት ለውጥ አስመልክቶ ያንጻባረቀችውን ሀሳብ በኮፕ 30 ላይ በአጀንዳንት ይዛ እንደምትቀርብ ጠቁመዋል።

በኮፕ 30 አረንጓዴ አሻራ እና በአካባቢ ጥበቃ እያከናወነቻቸው ያሉ ስራዎችን የሚያሳይ መካነ ርዕይ (ፓቪሊዮን) ለእይታ ክፍት እንደሚሆን አንስተዋል::

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም