በክልሉ ከ8 ሺህ በላይ የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ እና ጥገና ይከናወናል

ባህርዳር፤  ሐምሌ 1/2017 (ኢዜአ) ፡-  በአማራ ክልል በክረምት  የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ8 ሺህ በላይ የአቅመ ደካማ ቤቶችን  የመገንባት እና የመጠገን ስራ እንደሚከናወን ተገለጸ።  

ክልላዊ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር "በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሀሳብ በባህርዳር ከተማ ጣና ክፍለ ከተማ ዛሬ ተጀምሯል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት  የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እንደገለጹት፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የማህበረሰቡን እሴት መሰረት በማድረግ እየተከናወነ ይገኛል።


 

በጎ ፈቃደኞችም በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ፣ የአቅመ ደካሞችን መኖሪያ ቤት በመስራትና በመጠገን፣ የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት፣ የሰብል ልማትና ሌሎች ተግባራት ለማከናወን እንደተዘጋጁ አስታውቀዋል።

በዚህም በክልል ደረጃ ከ8 ሺህ በላይ የአቅመ ደካሞችን መኖሪያ ቤት ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ በመገንባትና በመጠገን የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ይደረጋል ብለዋል።  

ለዚህም የህዝብን አቅም ፣ የመንግስት እና  የልማት ድርጅቶች  ተሳትፎ  በማጎልበት ተፈጻሚ እንደሚሆን  ተናግረዋል።

በሁሉም የክልሉ ዞኖች፣ የከተማ አተዳደሮችና ወረዳዎች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ ዛሬ በይፋ መጀመሩን ይፋ አድርገዋል።

የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ  ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው፤   የዳበረ ባህላዊ እሴታችን የሆነውን በጎነትን   በመተግበር የብልፅግና ጉዞን እናረጋግጣለን ብለዋል።


 

የተጀመሩ ሰው ተኮር ስራዎችን በበጎ ፈቃድ ስራ በማጠናከር  ወገኖችን መደገፍ ይገባናል ሲሉ አመልክተዋል።

በከተማ  አስተዳደሩ ባለፈው ዓመት የክረምት ወራት 375 የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤቶችን በመገንባትና በማደስ ለተጠቃሚዎች ማስረከብ መቻሉን አውስተዋል።

በዘንድሮው ክረምትም ካለፈው ዓመት በተሻለ መልኩ የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤቶችን ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ ገንብቶ ለማስረከብ በቂ ዝግጅት መደረጉንም አስታውቀዋል። 


 

በክረምት በጎ ፈቃድ ክልላዊ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የፌዴራል፣ የክልል፣  የሰሜን ጎጃም ዞንና የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም