በአማራ ክልል ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ የሚያስችሉ ተግባራት ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ የሚያስችሉ ተግባራት ይጠናከራሉ

ባሕርዳር ፤ ሐምሌ 1/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የታክስ አስተዳደሩን በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርዓት በማዘመንና በማቀላጠፍ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ የሚያስችሉ ተግባራት እንደሚጠናከሩ ተገለጸ።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ከሐምሌ ጀምሮ በየዓመቱ የሚካሄደውን የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች የንቅናቄ መድረክ ማምሻውን በባሕር ዳር ከተማ አካሄዷል።
በመድረኩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ባደረጉት ንግግር፤ የክልሉን ልማት ለማፋጠን፣ ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈንና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ገቢን አሟጦ መሰብሰብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ለዚህም የታክስ አስተዳደሩን በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርዓት በማዘመን ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ ለመሰብሰብ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
ይህም አሰራሩን ቀልጣፋና ፍትሃዊ ማድረግ፣ የግብር ስወራን በመቆጣጠር፣ ህገ ወጥ ነጋዴዎችን ወደ ግብር መረቡ ማስገባት ላይ የአዲሱ በጀት ዓመት ትኩረት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለስኬታማነቱም በየደረጃው ያለው አመራር፣ የዘርፉ ባለሙያና ሌላው ባለድርሻ አካል በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ክብረት ማህሙድ በበኩላቸው፤ የክልሉ ኢኮኖሚ የሚያመነጨውን ገቢ በመሰብሰብ ለልማት በማዋል በኩል ቀደም ሲል አበረታች ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል፡፡
በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከተለያዩ የገቢ አርዕስቶች 58 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ በክልሉ ለሚካሄዱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ማዋል መቻሉን ገልጸዋል።
በተጀመረው አዲሱ የበጀት ዓመት በክልሉ የወጪ ፍላጎትን በራስ አቅም ለመሸፈን በገቢ አሰባሰቡ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።
ለዚህም አመራርና ባለሙያ እንዲሁም ግብር ግብር ከፋይ የሚጠበቅበትን በመክፈል ሁሉም ኃላፊነቱን በተገቢው ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በንቅናቄ መድረኩ ላይ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ ሌሎች የስራ ሃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።