ግብርን በአግባቡ በመክፈል ለሀገር ልማትና እድገት የምናደርገውን አስተዋጽኦ እናጠናክራለን- የንግዱ ማህበረሰብ አባላት - ኢዜአ አማርኛ
ግብርን በአግባቡ በመክፈል ለሀገር ልማትና እድገት የምናደርገውን አስተዋጽኦ እናጠናክራለን- የንግዱ ማህበረሰብ አባላት

ሐረር ፤ ሐምሌ 1/2017(ኢዜአ)፦ግብርን በአግባቡ በመክፈል ለሀገር ልማትና እድገት የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ እንደሚያጠናክሩ በሐረሪ ክልል የሚገኙ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ተናገሩ።
በሐረሪ ክልል ለታማኝና ከፍተኛ ግብር ከፋዮች እውቅና የመስጠት ስነ-ስርዓት ዛሬ ተካሄዷል።
በወቅቱም ታማኝና ከፍተኛ ግብር ከፋዮቹ እንደገለፁት፤ ግብርን በወቅቱና በአግባቡ በመክፈል ለሀገር ልማትና እድገት የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ አጠናክረው ይቀጥላሉ።
በከተማው በዓይን ህክምና እና በሌሎች ኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩት ዶክተር ኑረዲን አብዲ እንዳሉት ህዝቡ ለሚያነሳው የልማት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በግብር የሚሰበሰብ ገቢ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።
ግብር መክፈል “የውዴታ ግዴታ ነው” ያሉት ዶክተር ኑረዲን የተሻለች አገርን ለመገንባትና ለትውልድ ለማስተላለፍ ግብርን በወቅቱ መክፈል እንደሚገባና ለተሰጣቸውም እውቅና ምስጋና አቅርበዋል።
''ግብር የምንከፍለው ልማቱ ተሳልጦ የማህበረሰቡ ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ ነው'' ያሉት ደግሞ በከተማው በሆቴል ስራ የተሰማሩት አቶ ወንድሙ ፈይሳ ናቸው።
ግብር በመክፈሌ የዜግነት ግዴታዬን ተወጥቻለሁ፤ በዚህም ሽልማት ተበርክቶልኛል፤ ሁሉም የሚጠበቅበትን ግብር በወቅቱ በመክፈል ሀገራዊ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በከተማው በህክምና ሙያ ዘርፍ ላይ የተሰማሩት ዶክተር ኑረዲን አህመድ በበኩላቸው ግብርን በወቅቱ መክፈል የዜግነት ግዴታን ከመወጣት ባሻገር ለዜጎች የስራ እድልን ለመፍጠር ሚናው የጎላ በመሆኑ ሁሉም ሃላፊነቱን መወጣት አለበት ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ከ4 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ የክልሉን 63 በመቶ የልማት ወጪ የመሸፈን ስራ ለማከናወን ዕቅድ መያዙን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ያሲን አብዱላሂ ናቸው።
በተለይ በክልሉ ግብርን በአግባቡ ለሚከፍሉ ታማኝ ግብር ከፋዮችም ምስጋና አቅርበዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በክልሉ ግብር ከፋዩ ግብሩን በአግባቡ በመክፈል ግዴታውን እንዲወጣ አሳስበው ከታክስ ማጭበርበርና ግብር ስወራ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን በህግ አግባብ የመቅረፉ ተግባር ይጠናከራል ብለዋል።