የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ፕሮጀክት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ፕሮጀክት ነው

ሚዛን አማን፤ ሐምሌ 1/2017 (ኢዜአ)፡- የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ መገንባት የሕዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ትልቅ ፕሮጀክት ነው ሲሉ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።
የአውሮፕላን ማረፊያው የግንባታ ሥራ ያለበትን ደረጃ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች በስፍራው በመገኘት ተመልክተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦለት እየተገነባ ያለው የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ የመንገዱ ሥራው ከ1 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር በላይ አስፋልት ለብሷል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሚዛን አማን ከተማ እየተገነባ የሚገኘው ፕሮጀክቱ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በተመለከቱበት ወቅት እንደገለጹት፤ የአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታ በሕዝብ ጥያቄ መነሻ እየተገነባ ያለ ትልቅ ፕሮጀክት ነው።
የአካባቢውን የቱሪዝም አቅም ወደ ኢኮኖሚ በመቀየር ዘላቂ የሕዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
ቡና እና ቅመማ ቅመምን ጨምሮ ሌሎችም ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶችን የግብይት ሂደት ለማሳለጥ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነም ጠቅሰዋል።የግንባታ ሂደቱ ጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑን መረዳታቸውን ገልጸዋል።
በምልከታው የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሸ ዋጌሾ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራል ፣ የክልል እና የዞን የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።