ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አብሮነትን እና ትስስርን ለማጠናከር ጉልህ ሚና አለው- በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አብሮነትን እና ትስስርን ለማጠናከር ጉልህ ሚና አለው- በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች

ወላይታ ሶዶ ፤ ሐምሌ 1/2017(ኢዜአ)፦ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ባህሎችና ዕሴቶችን በማወቅ አብሮነትና ትስስርን ለማጠናከር እንደሚያስችል የአገልግሎቱ ተሳታፊ ወጣቶች ተናገሩ።
የ4ኛው ዙር ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በዛሬው ዕለት ወላይታ ሶዶ ከተማ የገቡ ሲሆን የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሄደዋል።
በወቅቱም ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ወጣቶች፤ በየአካባቢው የሚደረግላቸው አቀባበል የህብረተሰቡን የቆየ አብሮነት እሴት እንደሚያሳይና ይህም የእርስ በርስ ትስስርን ለማጠናከር እንዳስቻለ መገንዘባቸውን ተናግረዋል።
ከወጣቶቹ መካከል ወጣት ሐና ተስፋዬ ተግባሩ የሁሉም ክልል ወጣቶች ትስስራቸውን እንዲያጠናክሩ የሚያግዝ እንዲሁም ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን የሚያጎለብት መሆኑን ተናግራለች።
በመሆኑም አብሮነትን በማጠናከር ነገ የምንረከባትን ሀገር ዛሬ እየሰራን እንገኛለን ብላለች።
''ችግኝ በመትከል ለቀጣዩ ትውልድ የለመለመች ሀገርን ለማስረከብ የጀመርነውን ስራ ዘላቂ እንዲሆን እየሰራን ነው'' ያለው ወጣት ዮናስ ድማማው በበኩሉ በየተጓዙበት ሁሉ የህዝቡን ባህልና ወግ የማወቅ ዕድል ማግኘታቸውን ገልጿል።
በጎነት ለበርካታ ወገኖች መድረስ የሚያስችል ከመሆኑም ባሻገር በህዝቡ ዘንድ ትስስርን የሚፈጥር በመሆኑ የሚጠበቅበትን ለመወጣት መዘጋጀቱን ተናግሯል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የወጣቶች ዘርፍ ኃላፊ ማርቆስ ማቴዎስ የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶች ሀገራቸውን አውቀው ሌሎችንም እንዲያሳውቁ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።
ዛሬ በወላይታ ሶዶ ከተማ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ማካሄዳቸውን ጠቁመው በክልሉ በሚኖራቸው ቆይታ የተለያዩ የበጎ ፈቃድ ስራዎችን እንደሚያከናውኑም አስረድተዋል።
ከተጀመረ አራት ዓመት የሆነው የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃድ አገልግሎት በወጣቶች መካከል ትስስር በመፍጠር ለሀገራዊ መግባባት አስተዋጽኦ ማበርከቱን የገለፁት ደግሞ በሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ እንደገና ፈቃዱ ናቸው።
የጉዞው ዋና ዓላማም ወጣቶች በጎነትን ተለማምደው በወሰን ሳይገደቡ ለወገኖቻቸው እንዲደርሱ ማስቻል ነው ብለዋል።
ዘንድሮ ከ12 ክልሎች እና 2 ከተማ መስተዳድሮች በአጠቃላይ 112 ወጣቶች መሳተፋቸውን ጠቁመው በየዓመቱ እያደገ በመጣው በዚህ ስራ አብሮነትን የሚያጠናክሩ በርካታ ተግባራት እንደሚከናወኑም ተናግረዋል።