በክልሉ የፍራፍሬ እና የደን ችግኞችን በግል ማሳና የወል መሬት ላይ በማልማት ለዘላቂ ተጠቃሚነት መትጋት ይገባል

ባሕርዳር፤ሐምሌ 1/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የፍራፍሬ ፣ የደን እና የእንስሳት መኖ ችግኞችን   በግል ማሳና በወል መሬት  ላይ በመትከልና በማልማት  ለዘላቂ ተጠቃሚነት  መትጋት እንደሚገባ  የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር  አረጋ ከበደ አሳሰቡ።

"በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብ በሰሜን ጎጃም ዞን ይልማና ዴንሳ ወረዳ በአቦላ ተራራ ተፋሰስ ክልላዊ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር  የፌዴራልና የክልል  ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ ተጀምሯል።


 

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር  አረጋ ከበደ በመርሃ ግብሩ ባደረጉት ንግግር፤ ችግሮችን የምንሻገረው የተራቆቱ አካባቢዎችን በችግኝ ተከላ አረንጓዴ በማልበስ ሁለንተናዊ ልማትን ማፋጠን ስንችል ነው  ብለዋል።

ችግኝ በመትከል የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በመቋቋም  ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚቻል ህዝቡ ተገንዝቦ ለአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ሙሉ አቅሙን ተጠቅመን መስራት አለብን ሲሉ  ገልጸዋል።

የተተከለውን ተንከባክቦ ማሳደግ የሁሉም   ኃላፊነት መሆን እንዳለበትም አመልክተዋል።

በመርሃ ግብሩም የፍራፍሬ፣ የደንና የእንስሳት መኖ ችግኞችን  በግል ማሳና በወል መሬት  ላይ በመትከልና በማልማት ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መትጋት  እንደሚገባ ገልጸዋል።

በየደረጃው የሚገኘው አመራርና የዘርፉ ባለሙያም ሳይንሳዊ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን ለማስፈፀም  ሊረባረቡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የግብርና ሚኒስቴር በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርና ሌሎች የግብርና ስራዎች እያደረገ ያለው ድጋፍ ያመሰገኑት ርዕሰ መስተዳድሩ፤  በቀጣይም እገዛውን  አጠናክሮ እንዲቀጠልም አመልክተዋል።

የግብርና ሚኒስትር  ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤልያስ በበኩላቸው፤  የደን ሀብትን  ጠብቆ ይበልጥ ለማሳደግ የተጀመረው ችግኝ ተከላ ተጠናክሮ መቀጠሉን  ገልጸዋል።


 

ባለፉት ሰባት ዓመታት እንደሀገር በአረንጓዴ አሻራ  የተተከለው  ችግኝ የፅድቀት ምጣኔውም 80 በመቶ ማድረስ መቻሉን አረጋግጠዋል።

ዛሬ በአማራ ክልል ይልማና ዴንሳ ወረዳ በአቦላ ተራራ ተፋሰስ የተተከለው ችግኝም የአካባቢው ሕብረተሰብ የቱሩፋቱ ተጠቃሚ እንዲሆን  ተንከባክቦ  እንዲያሳድግ መልእክት አስተላልፈዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል  የገጠር ክላስተር ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ  ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር ) ፤ በክልሉ ሁሉም አካባቢ ዛሬ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ በይፋ መጀመሩን  አስታውቀዋል።


 

ለችግኝ ተከላውም 1 ነጥብ 55 ቢሊዮን ችግኝ መዘጋጀቱን ጠቅሰው፤  ከዚህም ውስጥ  20 ሚሊዮን የሚሆነው ቡናን ጨምሮ የተለያዩ ፍራፍሬዎች እንደሆኑ  ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር  የተተከሉ ችግኞች የክልሉን መልካም ገፅታ ይበልጥ ከማጉላት  ባሻገር የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት በማሳደግ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል።

ክልላዊ የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃ  ግብር ላይ የፌዴራል፣ የክልልና የዞን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም