ኢትዮጵያ ለጎረቤቶቿ የምታቀርበው የአረንጓዴ ኃይል አማራጭ የአየር ንብረት ተጽዕኖን ለመከላከል ያላትን ጠንካራ ቁርጠኝነት የሚያመላክት ነው

 

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 1/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት እያቀረበች ያለው አረንጓዴ የኃይል አማራጭ የአየር ንብረት ተጽእኖን ለመከላከል እና ከባቢ አየርን ለመጠበቅ ያላትን ጠንካራ ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

17ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ በብራዚል ሪዮ ዴጄኔሮ ተካሄዷል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ በጉባኤው ላይ ተሳትፏል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ልዑኩ በጉባኤው ላይ የነበረውን ተሳትፎ አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ሚኒስትሯ በማብራሪያቸው ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል፥ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል እየተጠቀመቻቸው ያሉ የታዳሽ ኃይል አማራጮች ይገኝበታል።

ዓለም ላይ የአየር ንብረት ለውጥን አስመልክቶ በሚደረጉ ጉዳዮች ጎልተው ከሚሰሙ አጀንዳዎች መካከል ከብክለት ነጻ የኢነርጂ አጠቃቀም አንዱ እንደሆነ ገልጸዋል።

ብዙ ሀገራት አብዛኛው የኃይል ምንጫቸው ከበካይ ምንጮች መሆናቸውን ጠቅሰው፥ ይህም በአየር ንብረት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ አብዛኛውን የኤሌክትሪክ ኃይል የምታገኘው ከታዳሽ የኃይል ምንጮች እንደሆነ ተናግረዋል።

በተጨማሪም የፀሐይ፣የነፋስ እና ሌሎች የኢነርጂ አማራጮችን እየተጠቀመች እንደምትገኝም ነው ያነሱት።

በተለይም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከብክለት ነጻ የኃይል ምንጭ እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሯ፥ ለሀገሪቷ ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ምስራቅ አፍሪካ እና አጠቃላይ ለአፍሪካ ብርሃንን የሚሰጥ የኢነርጂ ምንጭ ነው ብለዋል።

ግድቡ እያመነጨ የሚገኘው ኃይል ዓለም የሚፈልገውን ከበካይ ምንጭ ነጻ የሆነ ኢነርጂ መሆኑን የበለጠ ተቀባይነቱን እንደሚያሳድገው ተናግረዋል።

በጥቅሉ ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ከብክለት ነጻ የሆነ ኢነርጂ በማቅረብ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በተግባር ማረጋገጧን አመልክተዋል።

አረንጓዴ ኢነርጂ የኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ምላሽ አካል መሆኑን ነው ሚኒስትሯ የገለጹት።

ኢትዮጵያ በቀጣዩ ዓመት በብራዚል በሚካሄደው 30ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 30) እና በሌሎች የአየር ንብረት ለውጥ መድረኮች በታዳሽ ኃይል ልማት እያከናወነች ያለችውን ስራ በስፋት እንደምታስተዋውቅ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም