የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በህብረት የመስራት እሴትን እያጠናከረ ነው-ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ - ኢዜአ አማርኛ
የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በህብረት የመስራት እሴትን እያጠናከረ ነው-ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ

ሠመራ፣ሐምሌ 1፣2017 (ኢዜአ) በአፋር ክልል እየተካሄደ ያለው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በህብረት የመስራት እሴትን ማጠናከሩን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉን የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን የአቅመ ደካማ ቤቶችን በማደስ አስጀምረዋል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይም ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት እየተካሄደ ያለው የክረምት ወቅት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በህብረት የመስራት እሴትን እያጠናከረ ነው።
ይህን በመጠቀም በዚህ ዓመት 170 ለሚሆኑ አቅመ ደካማ ወገኖች ቤት የማደስ ስራ እንደሚከናወን ገልፀው በሎጊያ ክፍለ ከተማ አራት ቤቶችን በማደስ ስራውን አስጀምረናል ብለዋል።
የህዝቡን የመተጋገዝ እና የመደጋገፍ ነባር እሴት በመጠቀም በክልሉ ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የወጣቶች ባህልና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሐሚድ ዱላ እንደ ሀገር በክረምት ወራት በ14 የተለያዩ የበጎ አድራጎት ዘርፎች ከ300 ሺህ በላይ ወጣቶች የሚሳተፉበት ስራዎች ይከናወናሉ ብለዋል።
በበጎ ፈቃድ ዘርፎቹም ወጣቶችን በንቃት በማሳተፍ ለሀገራቸው የበኩላቸውን ሚና የሚወጡበትን ተግባር ለማቀላጠፍ መሰራቱን አስረድተዋል።
አቅመ ደካማ ወገኖችን መርዳት የማህበረሰቡን የመተባበርና የመደጋገፍ ባህል ማጠናከር መሆኑን የገለፁት ደግሞ የሠመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አብዱ ሙሳ ናቸው።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የክልልና የከተማ አስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።