በክልሉ የቡናን የጥራት ደረጃ በማስጠበቅ የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የቡናን የጥራት ደረጃ በማስጠበቅ የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል
ቴፒ፤ ሐምሌ 1/2017(ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከቡና የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ለጥራቱ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ) ተናገሩ።
በክልሉ ቴፒ ከተማ የምርት ጥራት ምርመራና ሰርተፊኬሽን ማእከል የፌዴራል እና የክልሉ መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ክልሉ ለቡና ልማት ምቹና ሰፊ መሬት ቢኖረውም በዛው ልክ ከዘርፉ የሚገኘው ጥቅም ውስን መሆኑን ተናግረዋል።
ከቡና ምርት የሚገኘውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የጥራት ደረጃን ማሳደግ ላይ ትኩረት ተድርጎ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ለዚህም የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተቀረጹ ፓኬጆችን በመተግበር የክልሉን ብሎም ሀገራዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
በዚህ ሂደት ውስጥ የዓለም ገበያን ሰብሮ መግባት የሚችል ጥራት ያለው ቡና በማምረት ረገድ የዘርፉ ተዋንያን ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል።
ለክልሉ ሦስተኛ የሆነው የምርት ጥራት ምርመራና ሰርተፊኬሽን ማእከል ዛሬ በቴፒ ከተማ አገልግሎት መጀመሩ ለቡና አልሚዎችና አቅራቢዎች ትልቅ መነሳሳትን የሚፈጥር እንደሆነ አክለዋል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ዑመር፣ ባለፉት ዓመታት እንደ ሀገር የቡና ምርት ጥራት ምርመራና ሰርተፊኬሽን ማእከላትን ሰባት ማድረስ መቻሉን ጠቅሰዋል።
በቀጣይ ዓመት የማዕከላቱን ብዛት ወደ 13 ከፍ ለማድረግ እየተሰራ ሲሆን ይህም የቡና ጥራትን ለማስጠበቅ የሚደረገው ጥረት አንዱ አካል ነው ብለዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ጠቅሰው ዘንድሮ ከ400 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ወደ ውጭ ገበያ መላኩንም ተናግረዋል፡፡
ይህን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችሉ ተግባራት በየደረጃው ትኩረት ተሰጥቷቸው የሚሰሩ መሆኑን ነው የገለጹት።
በዞኑ ያለውን ሰፊ የቡና ልማት ውጤታማነት ለማረጋገጥ የማዕከሉ መከፈት አጋዥ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ ናቸው፡፡
በዞኑ ውስጥ ካለው ከ87 ሺህ ሄክታር በላይ የቡና ማሳ ውስጥ 60 ሺህ ሄክታሩ ምርት የሚሰጥ ሲሆን ከዚህም በየዓመቱ ከ55 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት እንደሚሰበሰብ ገልጸዋል።