ተረጂነትን ማስቀረት የሀገር ክብር እና የሉዓላዊነት ጉዳይ ነው-ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
ተረጂነትን ማስቀረት የሀገር ክብር እና የሉዓላዊነት ጉዳይ ነው-ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1/2017(ኢዜአ)፦ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈንና ተረጂነትን ማስቀረት የሀገር ክብርና የሉዓላዊነት ጉዳይ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን "90 ዓመታትን የተሻገረ የሰብዓዊ አገልግሎት አሻራ” በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል።
የማህበሩ የበላይ ጠባቂ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ማህበሩ በኢትዮጵያ ፈተናዎች የተወለደ የርህራሄና የበጎነት መገለጫ ነው ብለዋል።
የማህበሩ በጎ ተግባርም ከኢትዮጵያ የሉዓላዊነትና የሰብዓዊነት ተግባር ጋር የተቆራኘ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ዓለምአቀፍ የሰብዓዊነት ስምምነቶችን ከመቀበሏ በፊትም ህብረተሰቡ ሰብዓዊነትን በተግባር የኖረ የደግነትና የርህራሄ እሴትን መገለጫው ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ መርህ አልባነትና ኢ-ሰብዓዊነት እየጎላ መምጣቱን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፥ የሰብዓዊ ድጋፎች መቀዛቀዝም ዋና መገለጫው መሆኑን አስገንዝበዋል።
ይህን ታሳቢ በማድረግ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ቀጣይ ትኩረቱ የሰብዓዊ ተግባርን በራስ አቅም የማከናወን ዘላቂ አቅምን መገንባት ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በምግብ ራስን ለመቻል፣ በኢኖቬሽን ራሳችንን ለማብቃት እንደምንተጋው ሁሉ ተረጂነትን ማስቀረትና ለተጎዱ ወገኖቻችን በራስ አቅም ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ የክብር እና ሉዓላዊነት ጉዳይ አድርገን መስራት አለብን ብለዋል።
በቀጣይ ማህበሩ 100 ዓመቱን ሲያከብር፣ ህዝባዊ መሰረቱን አስፍቶ፣ በእሳቤ ጥራት፣ በገንዘብና በእውቀት ራሱን ችሎ፣ ዘመኑን የዋጀ ህጋዊ ማዕቀፍ አበጅቶ፣ ከኢትዮጵያ አልፎ በቀጣናውና በአፍሪካ የሰብዓዊነት ተምሳሌት የሆነ ታላቅ ተቋም ሆኖ ሊገኝ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ማህበሩ ባለፉት 90 ዓመታት ኢትዮጵያ ችግር ላይ በነበረችበት ወቅት ሁሉ ላከናወናቸው ሰብዓዊና የጀግንነት ተግባራት በኢትዮጵያ መንግስት ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የማህበሩ ፕሬዚዳንት አበራ ቶላ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በመላ ሀገሪቱ መዋቅሩን በማስፋት የሰብዓዊ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።
ማህበሩ ዓላማውን ለማሳካት የሚያስችለውን አቅም እየፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው፥ ለዚህ ደግሞ የመንግስት ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ነው ያነሱት።
ማህበሩ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት የአባላቱን ቁጥር 20 ሚሊየን በማድረስ ወጪውን በራስ አቅም የመሸፈን እቅድ መያዙንም አመልክተዋል።
የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ እንዲሁም ከማህበሩ ጋር የሚሰሩ አጋር ድርጅቶች የማህበሩን ያልተቋረጠና እያደገ የመጣ ሰብዓዊ ድጋፍን አድንቀዋል።
በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል በተከናወነው የበዓሉ ማጠቃለያ መርሃ-ግብር ማህበሩን ሲደግፉ የነበሩ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት እውቅና ተሰጥቷቸዋል።