ቀጥታ፡

የቡና ልማት ከአካባቢ ጥበቃ ሥራ ጋር መቀናጀቱን የሚያሳይ መረጃ በቴክኖሎጂ በማሰባሰብ ወደተደራጀ ሲስተም እየገባ ነው

ሀዋሳ፤ ሐምሌ 1/2017(ኢዜአ)፦ የቡና ልማት ከአካባቢ ጥበቃ ሥራ ጋር መቀናጀቱን የሚያሳይ መረጃ በቴክኖሎጂ በማሰባሰብ ወደ ሀገራዊ የተደራጀ ሲስተም እያስገባ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

ባለስልጣኑ ከሲዳማ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ለተውጣጡ የሚመለከታቸው አካላት በቡና ማሳ መረጃ አሰባሰብ ላይ ያተኮረ ስልጠና በሃዋሳ ከተማ እየሰጠ ነው፡፡


 

የባላስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለጹት ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ ከምታቀርበው ቡና  የምታገኘው ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መጥቷል፡፡

በኢትዮጵያ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር ምርት የሚሰጥ የቡና ማሳ መኖሩን የገለጹት ዳይሬክተሩ አብዛኛው የቡና ልማት ሥራ  በደን ውስጥ የሚከናወን መሆኑን ገልጸዋል፡፡

"ይህም 40 ከመቶ የሚሆነውን የቡና ምርት በሚቀበሉ የአውሮፓ አባል ሃገራት በኩል የውጡ አዳዲስ ህጎችና ደምቦችን ለመፈጸም ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል" ብለዋል፡፡

በቡና ልማቱ የተሰማሩ አምራቾችን ከማሳ እስከ ዓለም ገበያ ያለውን ሂደት የሚያሳይ መረጃ በአግባቡ ለማጠናቀር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ባለስልጣኑ የቡናን የአመራረት ሂደት የሚገልጽ መረጃ በቴክኖሎጂ አስደግፎ በማሰባሰብ ወደ ሀገራዊ የተደራጀ ሲስተም የማስገባት ሥራ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

የስልጠና መድረኩም የመረጃ አሰባሰብ ሂደቱን ውጤታማ በማድረግ ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርበውን የምርት ጥራት ለማስጠበቅ ያለመ መሆኑን አዱኛ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የልማት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ታጋይ ኑሩ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተጀመሩ ሥራዎች የመጣውን ውጤት ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡


 

አርሶ አደሩ ቡናን ሲያለማ ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት እንዲሰጥ ግንዛቤውን ከማሳደግ ጎን ለጎን ትኩረት ሰጥቶ እያለማ መሆኑን በቴክኖሎጂ የተደገፍ መረጃን የመሰብሰብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሲዳማ ክልል የቡና ልማት ስራው የደን ጭፍጨፋን በማስወገድ በጥምር ደን አሰራር እንደሚከናወን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ቡና፣ ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ቃሬ ናቸው።

በቡና ምርት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ቡናው የሚመረትበን ቦታ መረጃ የመሰብሰብና የመተንተን ሥራ በማህበራት፣ ዩኒየኖችና የግል ባለሃብቶች መከናወኑንም ጠቁመዋል፡፡


 

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የቡና ጥራት ቁጥጥር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ዘፈኔ ሌዛ በበኩላቸው፣ በዓለም ገበያ ውስጥ ያለንን ተወዳዳሪነት ለማስቀጠል  የቡና ልማት መረጃ አያያዝ ስልጠናው ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም በክልሉ ያለውን የቡና ማሳ መረጃ በተገቢው በመሰብሰብ በዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡


 

በስልጠናው ከሲዳማ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያና ማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ለተከታታይ ስድስት ቀናት በሚቆየው ስልጠና በቡና ማሳ መረጃ አሰባሰብ ላይ ያተኮረ የንድፈ ሃሳብና የተግባር ስልጠና እንደሚሰጥ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም