የአረንጓዴ አሻራ ልማት ለግብርና ምርትና ምርታማነት ማደግ ጉልህ ሚና እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ ልማት ለግብርና ምርትና ምርታማነት ማደግ ጉልህ ሚና እያበረከተ ነው

ወልቂጤ ፤ ሐምሌ 1/2017(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብር ስራዎች ለግብርና ምርትና ምርታማነት ማደግ ጉልህ ሚና እያበረከተ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) አመለከቱ።
ርዕሰ መስተዳድሩ ዛሬ በጉራጌ ዞን ጉመር ወረዳ አበኬ ቀበሌ ዌራ ንዑስ ተፋሰስ ላይ የ2017 ዓ.ም የክረምት ወቅት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በይፋ አስጀምረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተከናወኑ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች የግብርና ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ነው።
በዚህም የአፈር ለምነት መመለስና ማስጠበቅ እንዲሁም የደረቁ ምንጮች ማገገም መቻላቸውን አንስተው በተፈጥሮ ላይ የተሰራ ስራ በመሆኑ ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ ውጤት እያስገኘ ነው ብለዋል።
የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ በማድረግ ሳቢና ምቹ የመኖሪያ አካባቢዎች እንዲፈጠሩ ማድረጉን አመልክተዋል።
የክልሉ ህብረተሰብም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርን ባህል እያደረገ መምጣቱን ጠቅሰው የተጀመረውን ተፈጥሮን የመንከባከብ ስራ አጠናክሮ ሊያስቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳዳር ማእረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ስሩር በክረምት ወራት የአረንጓዴ አሻራ ልማት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ላላቸው የፍራፍሬ፣ የመኖ፣ የደን እና የቡና ችግኞች ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።
በክረምት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም ከ1 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ ገልፀው መትከል ብቻ ሳይሆን የተተከለው እንዲጸድቅ ተገቢ እንክብካቤ ሊደረግ ይገባል ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ዋና አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ሰርሞሎን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ካቢኔ አባላትና የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።