አገር የሚገነባው በተባበረ ሁለንተናዊ የህዝብ ተሳትፎ ነው -ሚኒስትር አህመድ ሽዴ - ኢዜአ አማርኛ
አገር የሚገነባው በተባበረ ሁለንተናዊ የህዝብ ተሳትፎ ነው -ሚኒስትር አህመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 1/2017(ኢዜአ)፦አገር የሚገነባው በተባበረ ሁለንተናዊ የህዝብ ተሳትፎ በመሆኑ ሁሉም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚጠበቅበት የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ፡፡
የ2017 አገር-አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ መጀመሩ ይታወቃል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር፣የፕላንና ልማት ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ አመራር አባላትና ባለሙያዎች እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የስራ ኃላፊዎች በእንጦጦ ፓርክ ዛሬ አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ አገር የሚገነባው በተባበረ ሁለንተናዊ የህዝብ ተሳትፎ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተገኘው ውጤት ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሮች የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መተከላቸውን ጠቁመው፥ይህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ እውቅና እንድታገኝ ማድረጉን ተናግረዋል።
በአረንጓዴ አሻራ ውጤት የተመዘገበው በከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ መሆኑንም አስረድተዋል።
አሁን ላይ በአገራችን ችግኝ ተክሎ መንከባከብ እና ማሳደግ የህብረተሰቡ ባህል እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡
ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት መንግስት ስትራቴጂዎችን ነድፎ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል አረንጓዴ አሻራ አንዱ መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ለሊሴ ነሜ በበኩላቸው፥የዛሬው የአረንጓዴ አሻራና የጽዱ ኢትዮጵያ መርሃ ግብር ዋና ዓላማ ጽዳትንና ውበትን ባህሉ ያደረገ ትውልድ ለመፍጠር ነው ብለዋል፡፡
በመላ አገሪቷ ጽዱ ኢትዮጵያን እውን የማድረግ የስድስት ወር ንቅናቄ በይፋ መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡
በአረንጓዴ አሻራና በጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ መርሃ ግብሮች ህብረተሰቡን በማሳተፍ የውሃ፣የአየርና የአፈር ብክለትን ለመከላከል እንደሚሰራ ነው የገለጹት።
የፌዴራል መንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሰረት መስቀሌ በበኩላቸው፤በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኞችን ከመትከል ባሻገር የጽድቀት መጠናቸውን ለመጨመር የመንከባከብ ስራ እንደሚሰራም አመልክተዋል፡፡
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን መትከል የህብረተሰቡን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
ከአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በተጨማሪም የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተመላክቷል፡፡