ቀጥታ፡

በክረምቱ ለሚያጋጥሙ ቅጽበታዊ አደጋዎች ምላሽ ለመስጠት በቂ ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1/2017(ኢዜአ)፦ በክረምቱ ለሚያጋጥሙ ቅጽበታዊ አደጋዎች ምላሽ ለመስጠት በቂ ዝግጅት መደረጉን የፌደራልና የክልል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽኖች ገለጹ።

ከክረምት ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ አደጋዎችን ለመቀነስ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።

በ2017/2018 የመኽር ወቅት ከመደበኛ እና መደበኛ በላይ የዝናብ ሁኔታ እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ትንበያ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደተናገሩት በሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ትንበያ መሰረት በክረምቱ የሚጠበቀው መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ለሰብል ስራና ውሃን ለመያዝ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው።


 

ከመደበኛ በላይ የዝናብ መጠን በሚያጋጥምባቸው አካባቢዎች የቅድመ ማስጠንቀቂያ መልዕክቶችን ለማህበረሰቡ የማድረስ ስራዎች በክልሎች በተጠናከረ መንገድ እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ለቅጽበታዊ አደጋዎች ምላሽ ለመስጠት በቂ ዝግጅት የተደረገ ሲሆን፥ ችግር ሊያጋጥማቸው በሚችሉ አካባቢዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት አስፈላጊ ቁሳቁሶች ከወዲሁ ተደራሽ ተደርገዋል ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት ወደ አስር የሚደርሱ ክልሎች ከፌደራል መንግስት ከሚላክላቸው መደበኛ ሰብአዊ ድጋፍ በመውጣት በራሳቸው መሸፈን እንደቻሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን ያላትን የተፈጥሮ ሃብትና አምራች የሰው ኃይል በመጠቀም እውን ለማድረግ ፖሊሲ ቀርጻ ተግባራዊ እያደረገች እንደምትገኝ አስታውሰዋል።

የአደጋ ምላሽ ፈንድ ማቋቋም፣ የእለት ደራሽና መጠባበቂያ ክምችትን መያዝ እንዲሁም ለቅጽበታዊ አደጋዎች የሚደረግ ዝግጅት ትኩረት ከተሰጣቸው መካከል ናቸው ብለዋል።

የ2017/2018 የመኽር ወቅት የሚኖረው የዝናብ መጠን በ2018 ዓ.ም ሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም ሙሉ ለሙሉ ለመሸፈን የተያዘውን እቅድ ለማሳካት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

የክልል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽኖች በበኩላቸው ሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን እያከናወኑ ያለውን ተግባር በመግለጽ ለክረምቱ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ተናግረዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሱሌማን አሊ ክረምትን ተከትሎ የሚያጋጥሙ የጎርፍ አደጋዎችን በዘላቂነት ለመከላከል የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በስፋት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ከዚህ ጎን ለጎን ቅጽበታዊ አድጋን ለመከላከል የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን ለማህበረሰቡ የማድረስ ስራ እየተከናወነ ሲሆን ሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

የአፋር ክልል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር መሃመድ ሁሴን በበኩላቸው፥ ክልሉ ሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን የተፈጥሮ ሃብትንና የሰው ኃይልን በመጠቀም ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።


 

በክልሉ ሊከሰቱ የሚችሉ ድንገተኛ የተፈጥሮ አደጋዎችን የስጋት ደረጃ በመለየት እንደ አስፈላጊነቱ ማህበረሰቡን ወደ ሌሎች አካባቢዎች የማዘዋወርና የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም