የአንድነትና የአብሮነት መገለጫ ለሆነው ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን- የፖሊስ አባላት - ኢዜአ አማርኛ
የአንድነትና የአብሮነት መገለጫ ለሆነው ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን- የፖሊስ አባላት
ጅማ፤ ሐምሌ 1/2017(ኢዜአ)፦የአንድነት እና የአብሮነት መገለጫ ለሆነው ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የጅማ ከተማ ፖሊስ አባላት ተናገሩ።
ዛሬ በጅማ ከተማ ፓሊስ መምሪያ ስር የሚገኙ የፖሊስ አባላት ከመደበኛ የጸጥታ ማስከበር ስራቸው በተጓዳኝ ለታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የቦንድ ግዢ በመፈጸም የልማት አጋርነታቸውን አሳይተዋል።
የፖሊስ አባላቱ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያዊያንን የበለጠ የሚያስተሳስር የልማት መሰረት መሆኑንም ጠቁመዋል።
የጅማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ዘላለም ነሞምሳ በወቅቱ እንዳሉት የፖሊስ አባላቱ ከመደበኛ የጸጥታ ማስከበር ስራቸው በተጓዳኝ በልማት ስራ ላይ በመሳተፍ አጋርነታቸውን ለማሳየት የቦንድ ግዢ መፈጸማቸውን ገልጸዋል።
የፖሊስ አባላቱ ባለፉት ዓመታት ለግድቡ ግንባታ በቦንድ ግዢ ሲሳተፉ መቆየታቸውን ገልጸው አሁንም የግድቡ ግንባታ ፍጻሜ ላይ መድረሱ በፈጠረላቸው ከፍተኛ ተነሳሽነት ተግባሩን ማስቀጠላቸውን ተናግረዋል።
ቦንድ ከገዙት የከተማው ፖሊስ አባላት መካካል ኮማንደር ክብረት ከበደ፣ ''ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የጋራ ሀብታችንና የአንድነታችን ምልክት በመሆኑ በቻልነው ሁሉ ድጋፋችንን እንቀጥላለን'' ብለዋል።
ኢንስፔክተር አርጋቸው በላይ በበኩላቸው፤ ''ሰላምና ጸጥታን ከማስከበር መደበኛ ስራችን ጎን ለጎን በልማት ስራዎችም እንሳተፋለን'' ሲሉ ገልጸዋል።
የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ ጣሃ ቀመር በበኩላቸው ''የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በአንድነት ከፍጻሜ ለማድረስ ሁላችንም መረባረብ አለብን'' ብለዋል።
''የከተማው ፖሊስ አባላትም የጋራ አሻራችን ያረፈበትንና የሀገራችን ኩራት የሆነውን ታላቁን የህዳሴ ግድብ ከፍጻሜ ለማድረስ እያደረጉ ያሉት እንቅስቃሴ የሚበረታታ ነው'' ሲሉ ገልጸዋል።
ከንቲባው አክለውም የከተማው ፖሊስ አባላት ከመደበኛ የጸጥታ ስራቸው በተጨማሪ በልማት ስራዎች የሚያደርጉት ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የህዳሴ ግድብ ገቢ ማሰባሰቢያ ዋንጫን ለክልሉ ዞኖችና ከተሞች የጸጥታ ዘርፍ አባላት ማስረከቡ ይታወሳል።
በዚሁ ጊዜ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ፤ የፀጥታ ሀይሉ በክልሉ አስተማማኝ ሰላም ለማረጋገጥ ከሚያደርገው ጥረት ባለፈ የህዳሴ ግድብ ከፍጻሜው እንዲደርስ እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን ከምክር ቤት አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የፊታችን መስከረም እንደሚመረቅ መናገራቸው ይታወቃል።