ለዜጎች ምቹ የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩና የማህበራዊ ዋስትና አገልግሎት እንዲስፋፋ ትኩረት ተሰጥቷል - ኮንፌድሬሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
ለዜጎች ምቹ የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩና የማህበራዊ ዋስትና አገልግሎት እንዲስፋፋ ትኩረት ተሰጥቷል - ኮንፌድሬሽኑ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1/2017(ኢዜአ)፦ በሀገሪቱ የኢንዱስትሪ ሠላም እንዲሰፍን ለዜጎች ምቹ የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩና የማህበራዊ ዋስትና አገልግሎት እንዲስፋፋ ትኩረት መስጠቱን የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ኮንፌድሬሽን(ኢ.አ.ፌ.ኮ) አስታወቀ።
የኮንፌድሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ፣ በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ እና በኢትዮጵያ የግል ድርጅት ሠራተኞች የጡረታ አዋጅ ላይ የስልጠና ወርክሾፕ እያካሄደ ይገኛል።
የኮንፌድሬሽኑ ፕሬዝዳንት ኢንጂነር ጌታሁን ሁሴን እንደገለጹት ኮንፌዴሬሽኑ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የዓለም አቀፍ አሠሪዎች ማህበር፣ የአፍሪካ አሠሪዎች ማህበር እና የኢጋድ ሪጅን አሠሪዎች ማህበር አባል በመሆን እየሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በየጊዜው ከተለያዩ አለም አቀፍ አሰሪዎች ማህበራት ጋር በሚያደርገው የሥራ ግንኙነት የኢትዮጵያን ገጽታ የሚገነቡ ሥራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የኢንዱስትሪ ሠላም እንዲሰፍንና የሠራተኛው መብት እንዲከበር፣ ለዜጎች ሰፊና ምቹ የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ እንዲሁም የማህበራዊ ዋስትና አገልግሎት እንዲስፋፋ እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በሥራ ቦታዎች የሙያ ደህንነትና ጤንነት እንዲጠበቅ፣ የሥራ ቦታዎች ከብክለትና ከብክነት ጽዱ ሆነው ለአረንጓዴ ልማት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የማድረግ ስራን እየሰራ እንደሚገኝ ጨምረው ገልጸዋል።
መድረኩ በሥራ ላይ ባሉት የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 እና የግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 1268/2014 ላይ በመወያየት የጋራ ግንዛቤ መያዝ የሚያስችል መሆኑንም አንስተዋል።
እንዲሁም በጠቅላላ ጉባኤው የጠቅላይ ምክር ቤት እና የቦርድ ስራ አስፈጻሚዎች ምርጫ እንደሚያካሄድም አመልክተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራና ክህሎት ቢሮ የአሰሪና ሰራተኞች ጉዳዮች ወሳኝ ቦርድ ዳይሬክተር ካሳ ስዩም በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ላይ ገለጻ ባደረጉበት ወቅት በአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ላይ በቂ ግንዛቤ መፍጠር ለዘርፉ ስኬት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
መድረኩ የኢትዮጵያ አሠሪ ፌዴሬሽኖች ከዓለም ሥራ ድርጅት(ILO) እና ከግል ድርጅት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።