ስሎቬኒያ ከኢትዮጵያ ጋር በፖለቲካ እና ኢኮኖሚው መስክ ያላትን ትብብር ማጠናከር ትሻለች - አምባሳደር ክሪስቲና ራዴጅ - ኢዜአ አማርኛ
ስሎቬኒያ ከኢትዮጵያ ጋር በፖለቲካ እና ኢኮኖሚው መስክ ያላትን ትብብር ማጠናከር ትሻለች - አምባሳደር ክሪስቲና ራዴጅ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1/2017(ኢዜአ)፦ ስሎቬኒያ ከኢትዮጵያ ጋር በፖለቲካ እና ኢኮኖሚው መስክ ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር የበለጠ ለማጎልበት እንደምትሻ በኢትዮጵያ የስሎቬኒያ አምባሳደር ክሪስቲና ራዴጅ ገለጹ።
ስሎቬኒያ እ.አ.አ ኖቬምበር 1/2024 በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን መክፈቷ ይታወቃል።
በኢትዮጵያ የስሎቬኒያ አምባሳደር ክሪስቲና ራዴጅ የኤምባሲው መከፈት ስሎቬኒያ ከኢትዮጵያ እና አፍሪካ ጋር ያላትን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትብብር ለማጎልበት ያላትን ስትራቴጂካዊ ቁርጠኝነት የሚያመላክት መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የዲሎማሲ ማዕከል ናት ያሉት አምባሳደሯ ኤምባሲው ስሎቬኒያ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር እና ለባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ስራዎች እንደሚያገለግልም አመልክተዋል።
ስሎቬኒያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከርና በቀጣናዊ ትስስርና የድህረ ግጭት መልሶ ማቋቋምና መልሶ ግንባታ ላይ ያላትን ልምድ ማካፈል እንደምትፈልግ ተናግረዋል።
በኢኮኖሚ እና ንግድ መስክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር እንደምትሻም ነው የገለጹት።
ግብርና፣ ታዳሽ ኃይልና ቴክኖሎጂ ስሎቬኒያ ከለየቻቸው የልማት መስኮች መካከል እንደሚጠቀሱ ገልጸው የስሎቬኒያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያሉ እድሎችን ለመመልከት የቅደመ-ኢንቨስትመንት ጉብኝቶች ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
ስሎቬኒያ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በግብርና ኢኖቬሽን ውጤቶች ላይ ያላትን ተሞክሮ ለኢትዮጵያ ማጋራት እንደምትፈልግም አምባሳደሯ ገልጸዋል።
እንደ አምባሳደሯ ገለጻ፤ ስሎቬኒያ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች አርሶ አደሮችና በግብርና ምርቶች ንግድ ላይ የተሰማሩ ዜጎችን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርጉ በሙከራ ደረጃ ላይ የሚገኙ የንብ ማነብ ስራ ፕሮግራሞችን እየደገፈች ነው።
እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያ እና ስሎቬኒያ የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ሀገራቸው ቁርጠኛ እንደሆነችም አመልክተዋል።
ስሎቬኒያ የአፍሪካን የቅድሚያ ትኩረቶች መሰረት ባደረገ መልኩ የአህጉሪቱ ትልሞች እንዲሳኩ ድጋፍ ማድረግ እንደምትፈልግ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እና ስሎቬኒያ በግንቦት ወር 2017 ዓ.ም ሶስተኛ የፖለቲካ ምክክራቸውን በአዲስ አበባ ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን በምክክሩም ሀገራቱ ያላቸውን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ትብብር ለማጠናከር ተስማማተዋል።
የስሎቬኒያ ፕሬዝዳንት ናታሻ ፒርች ሙሳር በግንቦት ወር 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ ያደረጉት ይፋዊ የስራ ጉብኝት የትብብሩ እያደገ መምጣት ማሳያ ነው።