የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በራስ አቅም የተመሰረተ ሰብዓዊ አሻራን ለማኖር ትኩረት ሊሰጥ ይገባል - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በራስ አቅም የተመሰረተ ሰብዓዊ አሻራን ለማኖር ትኩረት ሊሰጥ ይገባል - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በራስ አቅም የተመሰረተ ሰብዓዊ አሻራን ለማኖር ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ አስገነዘቡ።
ማህበሩ ባለፉት 90 ዓመታት ኢትዮጵያ ችግር ላይ በነበረችበት ወቅት ሁሉ ላከናወናቸው ሰብዓዊና የጀግንነት ተግባራት በኢትዮጵያ መንግስት ስም ምስጋና አቅርበዋል።
የማህበሩ 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓል "90 ዓመታትን የተሻገረ የሰብዓዊ አገልግሎት አሻራ” በሚል መሪ ሀሳብ ተከብሯል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የማህበሩ የበላይ ጠባቂ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ፣ የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች ሳህለወርቅ ዘውዴና ሙላቱ ተሾመ(ዶ/ር)፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶን ጨምሮ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
የማህበሩ የበላይ ጠባቂ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ማህበሩ በኢትዮጵያ ፈተናዎች የተወለደ የርህራሄና የበጎነት መገለጫ ነው ብለዋል።
የማህበሩ ተግባርም ከኢትዮጵያ የሉዓላዊነትና የሰብዓዊነት ተግባር ጋር የተቆራኘ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ስምምነቶችን ከመቀበሏ በፊትም ህብረተሰቡ ሰብዓዊነትን በተግባር የኖረ የደግነትና የርህራሄ እሴትን መገለጫው ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ማህበሩ የዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን ተቀብሎ የተቋቋመ መሆኑን ጠቅሰው ማህበሩ ገና ከመመስረቱ ኢትዮጵያ የገጠማትን የሉዓላዊነት ፈተና ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት የማህበሩ አባላት የአካልና የህይወት መስዋዕትነት ጭምር በመክፈል በጀግንነት እንደሚወሱ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስትም ለዚህ የሰብዓዊነት አሻራ ከፍተኛ ምስጋና እንዳለው ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ መርህ አልባነትና ኢ-ሰብዓዊነት እየጎላ መምጣቱን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፥ የሰብዓዊ ድጋፎች መቀዛቀዝም ዋና መገለጫው እየሆነ ነው ብለዋል።
ይህን ታሳቢ በማድረግ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ቀጣይ ትኩረቱ የሰብዓዊ ተግባርን በራስ አቅም የማከናወን ዘላቂ አቅምን መገንባት ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በምግብ ራስን ለመቻል፣ በኢኖቬሽን ራሳችንን ለማብቃት ቀን ከሌሊት እንደምንተጋው ሁሉ ተረጂነትን ለማስቀረትና የተጎዱ ወገኖቻችንን በራስ አቅም መደገፍ የሉዓላዊነት ጉዳይ አድርገን ማሰብ አለብን ብለዋል።
ለዚህም ከነባራዊው የእርዳታ ጥገኝነት በመላቀቅ የሰብዓዊ ተግባራትን በራስ አቅም የሚያሟላ ቁመና መገንባት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ለዚህ ደግሞ ምኞታችንን የሚመጥን የሀሳብ ጥራት፣ ግልፅ፣ ተጠያቂነትን የያዘ አሳታፊ አሰራርን መትከል ይኖርብናል ነው ያሉት።
በቀጣይ ማህበሩ 100 ዓመቱን ሲያከብር፣ ህዝባዊ መሰረቱን አስፍቶ፣ በእሳቤ ጥራት፣ በገንዘብና በእውቀት ራሱን ችሎ፣ ዘመኑን የዋጀ ህጋዊ ማዕቀፍ አበጅቶ፣ ከኢትዮጵያ አልፎ በቀጣናውና በአፍሪካ የሰብዓዊነት ተምሳሌት የሆነ ታላቅ ተቋም ሆኖ ሊገኝ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለማህበሩ ድጋፍ የሚያደርገው የማህበሩ ሰብዓዊ ዓላማዎች ከሀገራችን ነባር እሴቶች ጋር የተጣጣሙ በመሆናቸው ጭምር ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ በቀጣይም አስፈላጊውን ሁሉ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።
የማህበሩ ፕሬዚዳንት አበራ ቶላ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በመላ ሀገሪቱ መዋቅሩን በማስፋት የሰብዓዊ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።
ማህበሩ ዓላማውን ማሳካት የሚያስችለውን አቅም እየፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው፥ ለዚህ ደግሞ የመንግስት ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ነው ያነሱት።
ማህበሩ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት የአባላቱን ቁጥር 20 ሚሊየን በማድረስ ወጪውን በራስ አቅም የመሸፈን እቅድ መያዙንም አመልክተዋል።