በበጀት ዓመቱ ከ23 ሺህ በላይ ዜጎች በልምድ ባገኙት ክህሎት ተመዝነው የዕውቅና ሰርትፊኬት አገኙ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1/2017(ኢዜአ)፦ በበጀት አመቱ ከ23 ሺህ በላይ ዜጎች በልምድ ባገኙት ክህሎት ተመዝነው የዕውቅና ሰርትፊኬት ማግኘታቸውን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ።

በልምድ ለተገኘ ክህሎት እውቅና የመስጠት ተግባር በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ተገልጿል።

በስራና ክህሎት ሚኒስቴር የሙያ ደረጃ ስርዓተ ስልጠናና ብቃት ምዘና መሪ ስራ አስፈጻሚ ማርታ ወልዴ ለኢዜአ እንደገለጹት በልምድ ለተገኘ ክህሎት እውቅና የመስጠት አሰራር ተዘርግቷል፡፡

ይህንንም ተከትሎ በበጀት አመቱ እውቅና የሚሰጥበት የምዘና መመሪያ ተዘጋጅቶ በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነ አሰራር ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን አንስተዋል።


 

በዚህም በበጀት አመቱ ከ23ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች በልምድ ባገኙት ክህሎት ተመዝነው የዕውቅና ሰርትፊኬት ማግኘታቸውን ነው የተናገሩት።

ባለሙያዎቹ የሚፈልገውን እውቀት እና ክህሎት ማሟላታቸውን በተቀመጡ መስፈርቶች በመመዘን የዕውቅና ሰርተፊኬቱ እየተሰጠ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ይህም ለዜጎች በልምድ ባገኙት እውቀት ተመዝነው የብቃት ማረጋገጫ በማግኘት በስራቸው የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ምዘናው በመንግስት ቅድሚያ በተሰጣቸው ዘርፎችና ሙያተኞች በሚበዙባቸውና በገበያው ፍላጎት ላይ ትኩረት በማድረግ እየተሰጠ ነው ብለዋል።


 

በአሁኑ ወቅት በኮንስትራክሽን፣ በሆቴል ስራ፣ በዌልዲንግና በሌሎች ዘርፎች የምዘና ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ በገበያው ላይ ተፈላጊ የሆኑ 55 ሙያዎችን በመለየት የምዘና መስፈርቶች መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።

ተመዝነው ማለፍ ያልቻሉትን ክፍተት ባለባቸው ላይ ስልጠና በመስጠት በድጋሚ እንዲመዘኑና ዕውቅና እንዲያገኙ እንደሚደረግም ተናግረዋል።

እውቅና ያገኙ ባለሙያዎች በበኩላቸው በልምድ ባገኙት ክህሎት ተመዝነው ሰርትፊኬት ማግኘታቸው ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።

በግንባታ ስራ የተሰማሩት አቶ አስቻለው ሞላልኝ እና አቶ ይሁን በላይነህ ከዚህ በፊት በልምድ ባዳበሩት ሙያ ተመዝነው እውቅና ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ይህም ከቀደመው በተሻለ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸውና ሙያቸውን ለማሻሻል እንዳገዛቸው ነው የተናገሩት።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስር በሚገኙ የክልል የብቃትና ምዘና ኤጀንሲዎች ምዘናው እየተሰጠ በመሆኑ ዜጎች ብቃታቸውን ማረጋገጥ እንደሚችሉም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም