በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቀልጣፋ የግብር አሰባሰብ ስርዓት ተዘርግቷል - ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቀልጣፋ የግብር አሰባሰብ ስርዓት ተዘርግቷል - ቢሮው

ዲላ፤ ሐምሌ 1/2017(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቀልጣፋ የግብር አሰባሰብ ስርዓት መዘርጋቱን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ ከ83 ሺህ በላይ የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በቴሌ ብር እንደሚፈጽሙም ቢሮው ገልጿል።
በክልሉ በአሥር ቀናት ውስጥ ከደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ የግብር ክፍያ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ዛሬ በዲላ ከተማ አስተዳደር ሴሳ የታክስ ማዕከል ተካሂዷል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አለምነሽ ደመቀ በዚህ ወቅት ግብር ለህብረተሰቡ የልማት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ወሳኝ ነው ብለዋል።
በተለይ በክልሉ የሚገኙ ከተሞች ወጪያቸውን በራስ አቅም ሸፍነው የህዝቡን የልማት ጥያቄ መመለስ እንዲችሉ ግብር በአግባቡ መሰብሰብ ይገባቸዋል ነው ያሉት።
የደረጃ "ሐ" ግብር ክፍያ ዛሬ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች መጀመሩን ጠቁመው በዚህም ከ230 በላይ ገቢ መሰብሰቢያ ማዕከላት ክፍት መሆናቸውን ገልጸዋል።
በክልሉ ከ115 ሺህ በላይ የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች ይገኛሉ ያሉት ኃላፊዋ፣ ከእነዚህ ውስጥ ከ83 ሺህ በላይ የሚሆኑት ግብራቸውን በቴሌ ብር እንዲከፍሉ መመቻቸቱን ተናግረዋል።
ይህም ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝና ጊዜና ወጪን እንዲቀንስ ያስችላል ብለዋል።
ቀልጣፋ የግብር አሰባሰብ ሥርአት በመዘርጋቱም በቀጣይ አሥር ቀናት ውስጥ ብቻ ከደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ዛሬ ወደ ትግበራ ተገብቷል ነው ያሉት።
ግብርን በወቅቱና በታማኝነት መክፈል የስልጡን ማህበረሰብ መገለጫ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መስፍን ዴምሴ(ዶ/ር) ናቸው።
የዘንድሮው የደረጃ "ሐ" ግብር ክፍያን ከወትሮ በተለየ መልኩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዶ ከለሊቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ወደ ትግበራ ተገብቷል ብለዋል።
በከተማው ከሚገኙ ከ6ሺህ በላይ የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን ተናግረዋል።
ከግብር ከፋዮች መካከል አቶ ጥላሁን ዘሪሁን በበኩላቸው ከ81ሺህ ብር በላይ ግብር በመክፈል ግዴታቸውን በወቅቱና በታማኝነት መክፈላቸውን ገልጸዋል።
ከአምና ጀምሮ ግብራቸውን በቴሌ ብር እየከፈሉ መሆኑን ገልጸው የግብር አከፋፈሉ መዘመኑ ጊዜያቸውን ለመቆጠብ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
የግብር ግዴታቸውን በወቅቱ መክፈላቸው ለአካባቢያቸው ልማት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ እንደሚያግዛቸውም ገልጸዋል።
በተሰማሩበት አነስተኛ ንግድ ሰርተው ካገኙት ገቢ ከ2ሺህ 700 ብር በላይ ዓመታዊ ግብር በመክፈላቸው መደሰታቸውን የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ሮማን ዘውዴ ናቸው።
ዛሬ ከሌሊቱ 12 ሰዓት ተገኝተው ቀዳሚ ግብር ከፋይ ተብለው እውቅና በማግኘታቸው ልዩ ስሜት እንደፈጠረባቸው ጠቅሰው፣ ይህም በቀጣይ ንግዳቸውን በማስፋፋት ግብራቸውን በአግባቡ ለመወጣት እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም የንግዱ ማህበረሰብና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።