ህፃናትና ወጣቶች በአካል እና በአዕምሮ ብቁ ሆነው እንዲያድጉ ከተማ አስተዳደሩ መሰረተ ልማቶችን የማሟላት ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ህፃናትና ወጣቶች በአካል እና በአዕምሮ ብቁ ሆነው እንዲያድጉ ከተማ አስተዳደሩ መሰረተ ልማቶችን የማሟላት ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1 /2017 (ኢዜአ)፦ ህፃናትና ወጣቶች በአካል እና በአዕምሮ ብቁ ሆነው እንዲያድጉ የከተማ አስተዳደሩ የስፖርት ማዘውተሪያ እና የህፃናት መጫወቻ ስፍራዎችን ግንባታ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዛሬ ማለዳ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ መሪ ሎቄ 40/60 ኮንዶሚኒየም አካባቢና በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ እና የህፃናት መጫወቻ ስፍራዎችን ዛሬ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ከተማ አስተዳደሩ 15ሺህ 960 ፕሮጀክቶችን ገንብቶ ማጠናቀቁን ተናግረዋል።
ግንባታቸው ከተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች መካከል 122 የስፖርት ማዘውተሪያ እና 1ሺህ 155 የህፃናት መጫወቻ ስፍራዎች መሆናቸውን ተናግረው፤ ይህም ህፃናትና ወጣቶች በአካልና በአዕምሮ ብቁ ሆነው እንዲያድጉ የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አስተዳደሩ የሚገነባቸው ፕሮጀክቶች ህፃናትና ወጣቶችን ታሳቢ ያደረጉ እንደሆኑም ከንቲባዋ ተናግረዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች መሰረተ ልማቶቹን በአግባቡ በመጠቀም ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ እንዳለበትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።