የአውሮፓ ህብረት አፍሪካ መር የሰላም ማስፈን ጥረቶችን እንደሚደግፍ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የአውሮፓ ህብረት አፍሪካ መር የሰላም ማስፈን ጥረቶችን እንደሚደግፍ ገለጸ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1/2017 (ኢዜአ)፦ የአውሮፓ ህብረት በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ሰላም እና እርቅን ለማምጣት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን አስታወቀ።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ከአውሮፓ ህብረት የሳሄል ልዩ ተወካይ ጆአ ክራቪንሆ እና ከህብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ አኔት ዌበር (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል።
ሁለቱ ወገኖች እየተለወጠ በመጣው የሳሄል ቀጣና እና የአፍሪካ ተለዋዋጭ የደህንነት ሁኔታዎች ላይ የሀሳብ ልውውጥ አድርገዋል።
የቀጣናው ችግሮች ቀጣናዊ መፍትሄዎች እንዲያገኙ የማድረግ ጥረትን በተቀናጀ የባለብዝሃ ወገን የተግባር ምላሽ መደገፍ እንደሚገባም አንስተዋል።
የአውሮፓ ህብረት የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ግጭትን በመከላከል ዲፕሎማሲ (preventive diplomacy) ያላቸውን ጠንካራ አመራር ሰጪነት አድንቀዋል።
የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ህብረት መር አህጉራዊ የእርቅ፣ የማረጋጋት እና የግጭት መፍታት ጥረቶችን ለመደገፍ ቁርጠኛ እንደሆነ መግለጻቸውን ኢዜአ ከህብረቱ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።