በዞኑ የገቢ አቅምን በማሳደግ እየጨመረ የመጣውን የህዝብ የልማት ፍላጎት ለማሟላት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የገቢ አቅምን በማሳደግ እየጨመረ የመጣውን የህዝብ የልማት ፍላጎት ለማሟላት እየተሰራ ነው

ቦንጋ፤ ሰኔ 30/2017 (ኢዜአ)፡-በካፋ ዞን የገቢ አቅምን በማሳደግ እየጨመረ የመጣውን የህዝብ የልማት ፍላጎት ለማሟላት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
በዞኑ በ2017 በጀት ዓመት ለመሰብሰብ የታቀደውን 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ሙሉ በሙሉ ማሳካት መቻሉን የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል።
የዞኑ ገቢዎች መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2018 የደረጃ "ሀ"፣ "ለ" እና "ሐ" ግብር ከፋዮች የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ እንደገለጹት በዞኑ የገቢ አቅምን በማሳደግ እየጨመረ የመጣውን የህዝብ የልማት ፍላጎት ለማሟላት እየተሰራ ነው።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በዞኑ 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸው፣ በሁሉም ደረጃ በተደረገ ርብርብ ዕቅዱን ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።
ለአፈጻጸሙ መሳካት የገቢ መስሪያ ቤቱ ባለሙያዎችና አመራሮች እንዲሁም የባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ ነው።
በ2018 በጀት ዓመትም የገቢ አሰባሰብ አቅምን በእጥፍ በማሳደግ 5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት በርብርብ መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የግብር ከፋዮን ግንዛቤ በማሳደግና ህግ የማስከበር ሥራ ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ገቢን በወቅቱና በተገቢው መንገድ መሰብሰብ ይገባል ሲሉም አቶ እንዳሻው አሳስበዋል።
የገቢ አሰባሰብ ሥራን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና ገቢዎች መምሪያ ሀላፊ አቶ ደምመላሽ ንጉሴ ናቸው።
በዞኑ በ2017 በጀት ዓመት 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት መቻሉን ጠቁመው፣ ይህም አምና ከተገኘው ገቢ ጋር ሲነጻጸር ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።
ዘንድሮ ይህን በእጥፍ በማሳደግ የዞኑን ወጪ ከ64 በመቶ በላይ በራስ አቅም ለመሸፈን እንደታቀደ አቶ ደምመላሽ ገልጸው፣ ገቢን የመሰብሰብ ሥራው ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ ታግዞ ይከናወናል ብለዋል።
ዕቅዱን ለማሳካት የድጋፍና ክትትል ስራዎችን ማጠናከር፣ የወጡ አዳዲስ ህጎችን በሙሉ አቅም መተግበር፣ የሰው ሀይል እጥረትን መቅረፍ፣ የግብር ከፋዮችን ደረጃ ማሻሻል፣ ውዝፍ እዳን ማስመለስና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ገልፀዋል።
በቦንጋ ከተማ በአትክልትና ፍራፍሬ የንግድ ሥራ ላይ የተሰማራው ኑሮ አባመጫ፣ ግብር መክፈል የሀገር ልማትን መደገፍና በተዘዋዋሪ ራስን የሚጠቅም መሆኑን ገልጿል።
ግብር የምንከፍለው ሰርተን ካገኘነው ትርፍ ላይ ነው ያለው ደግሞ በፍራሽ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማራው ሌላኛው ግብር ከፋይ መሳፍንት ሲሳይ ነው።
ግብር የተሻለች ሀገር ለመገንባት ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም ግብር ከፋይ ሀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በግብር አፈጻጸም ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ የወረዳና የከተማ አስተዳደር መዋቅሮች ሽልማት የተበረከተ ሲሆን እውቅናም ተሰጥቷቸዋል።
በዞኑ ከ19 ሺህ በላይ የደረጃ "ሀ"፣ "ለ" እና "ሐ" ግብር ከፋዮች ያሉ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 86 በመቶ የሚሆኑት በደረጃ "ሐ" ላይ የሚገኙ ግብር ከፋዮች መሆናቸውን ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።