የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የሁለትዮሽ ውይይቶች ሀገራት ኢትዮጵያ በስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ያላትን ፍላጎት እና አቋም እንዲረዱ ያስቻለ ነው - ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የሁለትዮሽ ውይይቶች ሀገራት ኢትዮጵያ በስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ያላትን ፍላጎት እና አቋም እንዲረዱ ያስቻለ ነው - ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30 /2017(ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከ17ኛው የብሪክስ መሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ከሀገራት መሪዎች ጋር ያደረጓቸው የሁለትዮሽ ውይይቶች ኢትዮጵያ በስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ያላትን ፍላጎትና አቋም እንዲረዱና እንዲደግፉ ያስቻለ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) ገለጹ።
በብራዚል ሪዮ ዴጄኔሮ እየተካሄደ ባለው 17ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ልዑካቸው ተሳትፈዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) 17ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም ከጉባኤው ጎን ለጎን ከሀገራት መሪዎች ጋር የተደረጉ ውይይቶች የሁለትዮሽ ትብብርን ለማጠናከርና የሀሳብ ልውውጥ ለማድረግ ያስቻለ መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በተለያዩ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ያላትን ፍላጎትና አቋም ሀገራቱ እንዲረዱና እንዲደግፉ ለማግባባት ጥሩ እድል መፍጠሩንም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከብራዚል ፕሬዝዳንት ኢግናሲዮ ሉላ ዳሲልቫ ጋር ባደረጉት ውይይት የሁለትዮሽ በተለይም የኢኮኖሚ ትብብርን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሀሳብ መለዋወጣቸውን አመልክተዋል።
ውይይቱ የብራዚሉ ፕሬዝዳንት የኢትዮጵያን አቅጣጫ እና ፖሊሲ በአግባቡ እንዲረዱ ለማድረግ ጥሩ እድል መፍጠሩንም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ ጋር የሁለቱን ሀገራት ጠንካራ ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውንም ጠቅሰዋል።
የኢኮኖሚ እና ኢንቨስትመንት ትብብሩን ማጠናከር በውይይቱ አጽንኦት የተሰጠው ጉዳይ እንደሆነም ገልጸዋል።
ቻይና በኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ዘርፍ ያላትን አዎንታዊ አስተዋጽኦ የምታጠናክርበትን ሁኔታ በፓሪስ ክለብ ማዕቀፍ ውስጥ ቻይና ከፈረንሳይ ጋር በመሆን የኢትዮጵያ እዳ ላይ ሽግሽግ እንዲደረግ የተወጣችውን ከፍተኛ ሚና አጠናክራ ማስቀጠል በምትችልባቸው ሁኔታዎች ላይ መምከራቸውን አንስተዋል።
ቻይና በቅርቡ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት ከቀረጥ ነጻ ሸቀጥ ና ኤክስፖርት ማስገባት የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸቷና የሰጠችውን እድል አስመልክቶ የሀሳብ ልውውጥ መደረጉንም ሚኒስትሩ አንስተዋል።
የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ቡና ምርት በስፋት ወደ ቻይና እየገባ እንደሚገኝ ጠቅሰው የሀገራቱን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙንት ማጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ስሪል ራማፎሳ ጋርም የሁለትዮሽ ምክክር አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅን ለፕሬዝንዳቱ አብስረዋል ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በግድቡ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል ሀገራት ልምድ፣ ቴክኖሎጂና ኢንቨስትመንት ማግኘት ትፈልጋለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገሪቱ በትብብር ማዕቀፉ አስተዋጽኦ የምታበረክትባቸው ዘርፎች እንዳሉ ገልጸዋል።
ውይይቶቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከሀገራቱ ጋር ላለው ትብብር የሰጡትን ትኩረት እንደሚያመላክት ጠቅሰው ብሪክስ የጋራ ትብብርን ማጠናከር የሚያስችል ቁልፍ ማዕቀፍ እና አደረጃጀት መሆኑን አክለዋል።