ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ እርስ በርስ ለመተዋወቅና አብሮነትን ለማጠናከር ዕድል ፈጥሮልናል -- ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ እርስ በርስ ለመተዋወቅና አብሮነትን ለማጠናከር ዕድል ፈጥሮልናል -- ወጣቶች

ሀዋሳ፤ ሰኔ 30/2017 (ኢዜአ)፡- ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እርስ በርስ ለመተዋወቅና አብሮነትን ለማጠናከር ዕድል እንደፈጠረላቸው በአገልግሎቱ እየተሳተፉ ያሉ ወጣቶች ተናገሩ።
ወሰን ተሸጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ ወጣቶች በመሳተፍ የተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተግባራትን የሚያከናውኑበት ነው።
በአሁኑ ወቅትም በ2017 የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ሀዋሳ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ህብረተሰቡንና ሀገርን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎችን ወጣቶች በማከናወን ላይ ናቸው።
በሀዋሳ ከተማ አገልግሎቱን እየሰጡ ያሉ ወጣቶች ለኢዜአ እንደገለጹት ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፍቃድ አገልግሎት ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢ ከመጡት ወጣቶች ጋር ስለሚያገናኝ አብሮነትን ለማጠናከር ዕድል ፈጥሮላቸዋል።
ከአገልግሎቱ ተሳታፊዎች መካከል ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመጣው ወጣት ደሳለኝ ማሞ፣ ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ድንቅ እሴቶች ባለቤት መሆኗን ጠቁሞ፣ ለበጎ አገልግሎት ሥራው በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ከህብረተሰቡ ፍቅርና አክብሮትን መማሩን ተናግሯል፡፡
ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች መምጣታችን አንዱ የሌላውን ወግና ባህል ለማወቅ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል ያለው ወጣቱ፣ አገልግሎቱ ለሀገር ልማት በአንድነት ለመነሳት እንዳስቻላቸው ተናግሯል።
ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመጣችው ወጣት ኤልሳቤት ኢዮብ በበኩሏ በጉዞዋ ለአገልግሎት ስለሚሄዱባቸው አካባቢዎች በማህበራዊ ሚዲያ ከሰማችው የተለየ የሰላም ሁኔታ እንዳስተዋለች ተናግራለች።
ለአገልግሎት በተንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች አብሮነት እና ህብረብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ያገኘችውን ተሞክሮ ወደ አካባቢዋ ስትመለስ ለሌሎች ወጣቶችን እንደምታጋራም ገልጻለች።
የክረምት ጊዜዋን ሀገርና ህዝብን የሚጠቅሙ ተግባራትን በማከናወን በማሳለፏ ደስተኛ መሆኗንም ወጣት ኤልሳቤት ተናግራለች።
ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመጣው ወጣት ሚስባህ ናስር በበኩሉ፣ "በጎ ሥራ በክፍያ ሊተመን አይችልም ከዚያም በላይ የህሊና እርካታና እፎታን ይሰጣል" ብሏል።
በበጎ አገልግሎት ተግባሩ ከሁሉም አካባቢዎች ከመጡ ወጣቶች ጋር ለመገናኘትና ጥሩ ወዳጅነት ለመፍጠር መቻሉን ገልጾ፣ አገልግሎቱ ከሚያከናውኑት የልማት ሥራ በተጨማሪ ህብረብሔራዊ እንድነትን ለማጠናከር እያገዛቸው መሆኑን ተናግሯል፡
በአሁኑ ወቅትም ከሁሉም ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ 102 በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በሁለት ቡድን ተከፍለው ወደተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በመጓዝ አገልግሎቱን እየሰጡ ይገኛሉ።
ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ወደሃዋሳ ከተማ የመጡ ወጣቶች በከተማዋ የጽዳት ሥራ በማከናወንና ደም በመለገስ የአገልግሎት ሥራቸውን መጀመራቸው የሚታወስ ነው።