በሀገሪቱ በተከናወነ የተቀናጀ የበረሃ አንበጣ መከላከል ሥራ ውጤት እየተገኘ ነው - ግብርና ሚኒስቴር

አርባ ምንጭ፤ ሰኔ 30/2017(ኢዜአ)፦ በሀገሪቱ በተከናወነ የተቀናጀ የበረሃ አንበጣ መከላከል ሥራ ውጤት እየተገኘ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ባለፉት አምስት ዓመታት በተቀናጀ የበረሃ አንበጣ መከላከል ሥራ ከ1 ሚሊዮን በላይ አርሶና አርብቶ አደሮች ተጠቃሚ ሲሆኑ ከ505 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይም የኬሚካል ርጭት መደረጉን ሚኒስትሩ አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ በአምስት ዓመት የበረሃ አንበጣ መከላከልና መቆጣጠር ተግባር አፈጻጸም ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአርባ ምንጭ ከተማ እየመከረ ነው።

በግብርና ሚኒስቴር የፕሮጀክቱ ከፍተኛ የክትትልና ግምገማ ባለሙያ ኢያሱ ፀጋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት ከዓለም ባንክ በተገኘ 123 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ፕሮጀክት ተቀርጾ ሲተገበር ቆይቷል።

በዚህም የሰባት ዓመት የተቀናጀ የአንበጣ መከላከልና የተጎዱ አካላትን መልሶ የማቋቋም ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

ፕሮጀክቱ በዘጠኝ ክልሎች 311 ወረዳዎች በሚገኙ ከ1 ሚሊዮን በላይ አርሶና አርብቶ አደር ቤተሰቦችን ተጠቃሚ ማድረጉንም አቶ ኢያሱ አመልክተዋል።

በበረሃ አንበጣ መንጋ ተጎጂ ለሆኑ ወገኖች ከ168 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር፣ ከ180ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ እና ከ18 ሺህ ኩንታል በላይ የመኖ ዘር ድጋፍ ተደርጓል።

ከዚህ ጎን ለጎን በተጠቀሱ ወረዳዎች በአይሮፕላን በተደረገ የኬሚካል ርጭትና አሰሳ ሥራ ከ505ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከአንበጣ መንጋ መከላከል ተችሏል ብለዋል።

በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተከናወነ የተቀናጀ የበረሃ አንበጣ መከላከል ሥራ ውጤት እየተገኘ መሆኑንም አቶ ኢያሱ አስታውቀዋል።

በሚኒስቴሩ የበረሃ አንበጣ መከላከል ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ዘብዴዎስ ሳላቶ በበኩላቸው በሀገሪቱ የተቀናጀ የበረሃ አንበጣ መከላከል ሥራው እየተጠናከረ መምጣቱን ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ ባደረገው ተከታታይነት ያለው ቅድመ መከላከል ሥራ እንዲሁም ሰብላቸው የተጎዳባቸው ወገኖችን በተለያየ መንገድ በመደጎም ጉልህ ሚና ሲጫወት መቆየቱን ገልጸዋል።

በፕሮጀክቱ ቀሪ ሁለት ዓመታት የበረሃ አንበጣ ክስተትን አስቀድሞ ለመከላከል ከዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ በሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ ኮምቦልቻ፣ በምስራቅ ኢትዮጵያ ድሬዳዋ እንዲሁም በደቡብ ኢትዮጵያ አርባ ምንጭ ከተሞች የቅድመ ማስጠንቀቂያ ማዕከላት ግንባታ ለማከናወን ትቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የበረሃ አንበጣ መንጋ በሰብልና በዕፅዋት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከማድረስ ባለፈ ምርትና ምርታማነት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል ያሉት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትልና የእርሻ ዘርፍ ሃላፊ አድማሱ አወቀ ናቸው።

ባለፉት ጊዜያት በክልሉ በአንበጣ መንጋ ጉዳት የደረሰባቸው ከ25 በላይ ወረዳዎች መልሰው እንዲያገግሙ በየደረጃው ካሉ መዋቅሮች ጋር በተከናወነ ቅንጅታዊ ሥራ ለውጥ ተመዝግቧል ብለዋል።

ለአራት ቀናት በሚቆየው የግምገማ መድረክ ላይ የግብር እና የገንዘብ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ተወካዮችን ጨምሮ ከሁሉም ክልሎች የዘርፉ ተጠሪ አካላት እንዲሁም የዓለም ባንክ ተወካዮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም