በክልሉ በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ160ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ይለማል - አቶ ኡስማን ሱሩር - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ160ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ይለማል - አቶ ኡስማን ሱሩር

ወልቂጤ፤ ሰኔ 30/2017(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ160ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እንደሚለማ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ሱሩር ገለጹ።
በክልሉ ነገ የሚጀመረውን ክልል አቀፍ የ2017 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በማስመልከት መግለጫ ተሰጥቷል።
ክልላዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ነገ በጉራጌ ዞን ጉመር ወረዳ እንደሚጀመር ተመላክቷል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ሱሩር በመግለጫቸው እንዳስታወቁት በመርሃ ግብሩ ከ160ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ይለማል።
በዚህም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እንደሚተከሉ አስታውቀው በመርሀ ግብሩ በዋናነት የፍራፍሬና የቡና ችግኞች እንደሚገኙበት አስታውቀዋል።
ባለፉት ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የደን ሽፋንን በማሳደግ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን አስታውሰው ይህንኑ ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ ችግኞች የጽድቀት መጠን በማደጉ የመሬት ለምነትና የውሃ አካላት መጨመር እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ ጉልህ ፋይዳ አበርክቷል ሲሉም አክለዋል።
የክልሉ ደንና አካባቢ ጥበቃ ልማት ቢሮ ሃላፊ አብረሃም መጫ በበኩላቸው በክልሉ የችግኝ ተከላና እንክብካቤ ስራ ባህል እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።
የክልሉ ህዝብ ነገ በሚጀመረው ክልል አቀፍ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ በንቃት እንዲሳተፍም ጥሪ ቀርቧል።