በበጀት ዓመቱ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ የሚያስረዱና ከሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክሩ የፓርላማ ዲፕሎማሲ ሥራዎች ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በበጀት ዓመቱ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ የሚያስረዱና ከሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክሩ የፓርላማ ዲፕሎማሲ ሥራዎች ተከናውነዋል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2017(ኢዜአ)፦ በ2017 በጀት ዓመት የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ የሚያስረዱና ከሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክሩ የፓርላማ ዲፕሎማሲ ሥራዎች መከናወናቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ ገለጹ።
ምክትል አፈ ጉባኤዋ ይህን ያሉት ምክር ቤቱ ባካሄደው 3ኛ ልዩ ስብሰባ ላይ የበጀት ዓመቱን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ሲያቀርቡ ነው።
በዚሁ ወቅት በምክር ቤቱ ባሉ 16 የወዳጅነት ቡድኖች የተለያዩ የፓርላሜንታዊ ዲፕሎማሲ ሥራዎች መሰራታቸውን ነው ያብራሩት።
ከዚህ ውስጥ የምክር ቤት ከፍተኛ አመራሮች በጄኔቫ በተደረገ የዓለም ፓርላማ ኅብረት(IPU) ላይ መሳተፋቸውንና ከደቡብ ሱዳንና ናሚቢያ ከመጡ የፓርላማ አባላት ጋር የልምድ ልውውጥ መደረጉን ገልጸዋል።
በኡጋንዳ በተካሄደ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት የፓርላማ ትብብር ጉባኤ ላይ የተሳተፉ የቋሚ ኮሚቴ አባላት ኢትዮጵያ በግብርናና በምግብ ራስን ለመቻል እያደረገች ስላለው ስኬታማ ስራዎች ማስረዳታቸውን አንስተዋል።
በቋሚ ኮሚቴ ደረጃና በወዳጅነት ቡድኖች ከሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ዘርፈ ብዙ ስራዎችን መሰራታቸውንም ተናግረዋል።
በዚህም በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂና ጤናን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የልምድ ልውውጦች መደረጋቸውን ነው ያነሱት።
በበጀት ዓመቱ የኢትዮ-ፈረንሳይ፣ ኢትዮ-እስራኤል፣ ኢትዮ-አዘርባጃን፣ ኢትዮ-ደቡብ ኮሪያ፣ ኢትዮ-ጀርመን፣ ኢትዮ-ሞንጎሊያ፣ ኢትዮ-ኢራን፣ ኢትዮ-ፊንላንድ፣ ኢትዮ-ቻይና፣ የኢትዮ-ፓኪስታን፣ ኢትዮ-ካዛኪስታንና የኢትዮ-ስዊድን የወዳጅነት ቡድኖች ጋር ፍሬያማ ውይይቶች ተደርገዋል ብለዋል።
ከኢትዮ-ግሪክ የወዳጅነት ቡድን አባላት ጋር በፓርላማ ዲፕሎማሲ፣ በቴክኖሎጂ፣ በባህር ትራንስፖርት፣ በቱሪዝምና ኮንስትራክሽን ዘርፍ አብሮ ለመሥራት ያለመ ውይይት መደረጉን አንስተዋል።
በበጀት ዓመቱ በምክር ቤት ደረጃ 3 እና በቋሚ ኮሚቴዎች 22 በድምሩ 25 የፓርላማ ልዑካን ቡድን፣ የወዳጅነት ቡድን እና ሀገራት ጋር የጠንካራ ዲፕሎማሲ ሥራዎች መከናወናቸውን እንዲሁ።