ሕግ የማውጣት፣ የክትትልና የሕዝብ ውክልና ሥራዎች ምክር ቤቱ ባስቀመጠው መመሪያ መሰረት መከናወኑን የመከታተል ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2017(ኢዜአ)፦ ሕግ የማውጣት፣ የክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም የውክልና ሥራዎች የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባስቀመጠው መመሪያ መሰረት መከናወናቸውን የመከታተል ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

ምክር ቤቱ ባካሄደው 3ኛ ልዩ ስብሰባ ላይ የበጀት ዓመቱ የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።


 

ሪፖርቱን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ ባቀረቡበት ወቅት ምክር ቤቱ ባሉት አደረጃጀቶች በእቅድ የያዛቸውን ሥራዎች በብቃት ለመፈፀም በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።

በተለይ ምክር ቤቱ በሕግ የተሰጠውን አራት ዋና ዋና ተልዕኮዎች ለማሳካት የሰራቸው ሥራዎች ውጤታማ ናቸው ብለዋል።

ምክር ቤቱ በሕገ-መንግሥቱ በተሰጠው ሥልጣንና ተግባር መሠረት ሕግ የማውጣት፣ የፌዴራል አስፈፃሚ አካላትን የመከታተልና የመቆጣጠር፣ የሕዝብ ውክልና ሥራ እና የፓርላማ ዲፕሎማሲ ተግባራትን ትኩረት በመስጠት ማከናወኑን አብራርተዋል።

ምክር ቤቱ ባሉት 13 ቋሚ ኮሚቴዎች በአስፈፃሚ አካላት እቅድ ላይ ክትትልና ድጋፍ ማድረጉንም በሪፖርቱ አንስተዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በዓመት ሁለት ጊዜ የሚያካሂዷቸው የምርጫ ክልል የውክልና ሥራም በአግባቡ እየተመራና ሕዝቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ እያገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

ሕጎች ከመፅደቃቸው በፊትም በየደረጃው ያሉ የምክር ቤቱ የሕግ ክፍል ባለሙያዎችና የቋሚ ኮሚቴ አባላት ዝርዝር ምርመራ እንደሚያደርጉበት አስታውቀዋል።

ከዚህ ባለፈ የአስረጂና የሕዝብ ውይይት መድረኮችን በማመቻቸት በህጎቹ ላይ ግልፅነት እንዲፈጠር ተደርጓል ነው ያሉት።

በበጀት ዓመቱ ምክር ቤቱ ባካሄዳቸው 43 መደበኛ እና ልዩ ስብሰባዎች ከ50 በላይ አዋጆችን መርምሮ ማፅደቁን ነው የገለፁት።

ምክር ቤቱ በ2017 በጀት ዓመት ለሀገርና ሕዝብ ሁለንተናዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ሕጎች መርምሮ ማፅደቁን አብራርተዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ የተልዕኮ ስራዎች የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገባቸውን ገልጸዋል።

ይሁንና ከውክልና ስራ ጋር ተያይዞ ህዝቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ላይ አስፈጻሚ አካላት የእርምት እርምጃ ከመውሰድ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ክፍተቶች በቀጣይ ዓመት በትኩረት ሊሰራባቸው ይገባል ብለዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ምክር ቤቱ የሚያወጣቸው ሕጎች በአግባቡ መፈፀማቸውን ኦዲት ማድረግ መጀመሩን አስታውቀዋል።

የምክር ቤቱ የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎችም በተቀመጡ አቅጣጫዎች መሰረት እየተመሩና የተጠያቂነት አሰራርም ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ ሕግ የማውጣት፣ የክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም የውክልና ሥራን ባስቀመጠው መመሪያ መሰረት እንዲከናወን የማድረግ ተግባር በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ በበጀት ዓመቱ በእቅድ የያዛቸውን ተግባራት ለማሳካት ያደረገው ርብርብ ውጤታማ እንደነበር ነው የገለጹት።

በቀጣዩ በምክር ቤቱ አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን የነበሩ ጥንካሬዎችን በማስቀጠል ያጋጠሙ ክፍተቶችን በመሙላት የተሻለ ሥራ ለመከወን ሁሉም አባላት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም