ኢትዮጵያ በጉባኤው ላይ ብሄራዊ ጥቅሟንና የገለልተኝነት መርህን አማክላ አቋሟን በሚገባ አንጸባርቃለች- ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በ17ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ብሄራዊ ጥቅሟንና የገለልተኝነት መርህን ማዕከል አድርጋ አቋሟን በሚገባ ማንጸባረቋን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ።

17ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ በብራዚል ሪዮ ዴጄኔሮ ተካሄዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ልዑካቸው በጉባኤው ላይ ተሳትፈዋል።

ሚኒስትሩ ጉባኤውን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሪዮ ዴጄኔሮ ያቀኑት በጉባኤው ላይ ለመሳተፍና ከሀገራት መሪዎች ጋር በመወያያት የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከርን ዓላማ በማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።

መሪዎቹ ከተወያዩባቸው አበይት አጀንዳዎች መካከል አካታች እና ፍትሃዊ የዓለም አስተዳደር ስርዓት እና ሪፎርም ይገኝበታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም እና የገለልተኝነት መርህን መሰረት በማድረግ ዓለም ሁሉንም አካባቢ ማቀፍ እንደሚገባው እና የአፍሪካ ድምጽ በሁሉም የዓለም ተቋማት እኩል መደመጥ እንዳለበት ማንሳታቸውን ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።

አፍሪካ ከመደመጥ ባሻገር ተሳትፎዋ ሊያድግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸውን አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደቡብ ለደቡብ ትብብርን ማጠናከርን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት የረጅም ጊዜ ስልጣኔ፣ ብዝሃ ባህል እና ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላትን የባህልና የኢኮኖሚ ትብብር ለማጠናከር እና ልምድ ለመቅሰም እንደምትሰራ ተናግረዋል።

ከኢኮኖሚ እና ከፋይናንስ ጋር በተገናኘም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ከብሪክስ ጋር ባላት ትብብር ተጠቃሚ እየሆነች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

የብሪክስ ልማት ባንክ አይነት የፋይናንስ ተቋም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ኢ-ፍትሃዊ የፋይናንስ እና የብድር አቅርቦት አማራጭ መሆናቸውንና ኢትዮጵያ ከዚህ ተጠቃሚ እንደምትሆን ነው ያነሱት።

ዲጂታላዜሽን እና ሰው ሰራሽ አስተውሎትም ሌላኛው የውይይት ርዕሰ ጉዳይ ነበር።

ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዲጂታል ዓለሙ ይዞ የመጣቸውን መልካም እድሎች የበለጠ መጠቀም እና ስጋቶችን ለመቀነስ በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ መናገራቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ሰፋፊ ስራዎችን እያከናወነች እንደምትገኝ እና በዘርፉ ከብሪክስ ሀገራት ጋር በትብብር መስራት እንደምትሻ ጠቅሰዋል።

ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከንግግር ባለፈ በተግባር ለዓለም ምሳሌ የሚሆን ስራ እያከናወነች መሆኑን ተናግረዋል።

ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በአጠቃላይ በብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተሳካ ተሳትፎ ማድረጓን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም