የጸጥታ ሃይሎች የተቀናጀ ስራና የህዝቡ ጠንካራ ትብብር በክልሉ አስተማማኝ ሰላም መፍጠር አስችሏል - ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ ሙሁመድ - ኢዜአ አማርኛ
የጸጥታ ሃይሎች የተቀናጀ ስራና የህዝቡ ጠንካራ ትብብር በክልሉ አስተማማኝ ሰላም መፍጠር አስችሏል - ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ ሙሁመድ

ጅግጅጋ፤ ሰኔ 30/2017(ኢዜአ)፦ የጸጥታ ሃይሎች የተቀናጀ ስራና የህዝቡ ጠንካራ ትብብር በክልሉ አስተማማኝ ሰላም መፍጠር ማስቻሉን የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ ሙሁመድ ገለጹ።
በክልሉ አስተማማኝ ሰላም እንዲኖር አስተዋጽኦ ካደረጉት የጸጥታ አካላት መካከል የሚሊሻ አባላት ላደረጉት አስተዋጽኦ በጅግጅጋ የእውቅና መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በስነ-ሥርዓቱ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ ሙሁመድ፤ ከለውጡ በኋላ በሶማሌ ክልል የልማት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።
የትኛውንም ልማት ለማከናወን ሰላም ወሳኝ መሆኑን አንስተው የክልሉን ሰላም አስተማማኝ በማድረግ ሂደት የጸጥታ አካላት ላደረጉት የላቀ አስተዋጽኦና ለህዝቡ ጠንካራ ትብብር አመስግነዋል።
የዛሬው መርሃ ግብርም ለዚሁ ተግባር እውቅና ለመስጠት መሆኑን ገልጸው የክልሉን ሁለንተናዊ ልማት ለማስቀጠል ሰላምን አስጠብቆ መዝለቅ አስፈላጊ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።
የክልሉ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ አብዲቃድር ረሺድ፤ የክልሉ የሚሊሻ ሀይል ሠላምን በማስጠበቅ ረገድ የላቀ ሚናውን መወጣቱንና እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም ሰላምና ጸጥታን ሌት ከቀን የማስጠበቅ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።