የልማት ማህበሩ በክልሉ የትምህርትና የጤና ተደራሽነትን ማጎልበት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የልማት ማህበሩ በክልሉ የትምህርትና የጤና ተደራሽነትን ማጎልበት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው

ባህርዳር፤ ሰኔ 30/2017 (ኢዜአ)፡- የአማራ ልማት ማህበር በክልሉ የትምህርትና የጤና ተደራሽነትን በሚያጎለብቱ ተግባራት ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑን ገለፀ።
ማህበሩ ያስገነባቸውን የማህበራዊ ተቋማት ሰሞኑን በሚያካሂደው "የአልማ ሳምንት" መርሃ ግብር ለማስመረቅ መዘጋጀቱን አመልክቷል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ማህበሩ በ667 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃቱን አስታውቋል።
የማህበሩ የስትራቴጂና ኢኖቬሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አበረ መኩሪያ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት አልማ የክልሉን የትምህርትና የጤና ተደራሽነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
ለዚህም በ2017 በጀት ዓመት 89 የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችንና 348 የ1ኛ ደረጃ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን በማስገንባት ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረጉን ተናግረዋል።
እንዲሁም 19 ህንጻዎች /ብሎኮች/ በጤና ተቋማትና 23 ህንጻዎች ደግሞ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ገንብቶ ማጠናቀቁን አስረድተዋል።
አስገንብቶ ያጠናቀቃቸውን የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ከሐምሌ 01 እስከ 15/2017 ዓ.ም ድረስ በሚያካሄደው "የአልማ ሳምንት" መርሃ ግብር ለማስመረቅ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
የተገነቡትን ከማስመረቅ ጎን ለጎንም በግንባታ ላይ የሚገኙትን ህብረተሰቡ እንዲጎበኛቸው በማድረግ ፈጥነው እንዲጠናቀቁ የማነሳሳት ስራ እንደሚከናወን አስረድተዋል።
በተጨማሪም ሳምንቱን አስመልክቶ በሚያስመርቃቸው ተቋማት ውስጥ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በማካሄድና ደም በመለገስ ተደማሪ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ገልፀዋል።
አልማ ከ2017 እስከ 2021 በስትራቴጂክ ዕቅድ ዘመኑ የትምህርት ጥራትና ተገቢነቱን ለማሻሻል 18 ሺህ 489 ከቅድመ አንደኛ እስከ 2ኛ ደረጃ የመማሪያ ክፍሎችን ለመገንባት አቅዶ እየሰራ ነው ብለዋል።
እንዲሁም 373 ጤና ኬላዎችና 50 ሆስፒታሎች በመገንባትና የውስጥ ቁሳቁሳቸውን የማሟላት ተግባር እንደሚያከናውንም ተናግረዋል።
በዕቅድ ዘመኑም ለ100 ሺህ ወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር ማህበሩ ግብ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ተገንብተው ለአገልግሎት ዝግጁ የሆኑት የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትም የስትራቴጂክ እቅዱ አካል መሆናቸውንም አስረድተዋል።
አልማ ከ2012 እስከ 2016 ባሉት አምስት ዓመታት ከአባላትና ከአጋር አካላት ባሰባሰበው ከ7 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ሃብት የትምህርትና የጤና ተቋማትን በማስገንባት ለአገልግሎት አብቅቷል።
ማህበሩ በስትራቴጂክ እቅዱ አሁን ያለውን 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን የአባላት ቁጥር ወደ 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን በማሳደግ የገንዘብ ምንጩን ለማስፋት እየሰራ መሆኑንም በመግለጫው አመላክቷል።