ምክር ቤቱ እንዲታረም የቀረበለትን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ አጸደቀ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2017(ኢዜአ)፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በልዩ ስብሰባው ከአሁን በፊት ውሳኔ የተሰጠበት ድንጋጌ እንዲታረም የቀረበለትን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ አፅድቋል፡፡

ምክር ቤቱ በ37ኛ መደበኛ ስብሰባው በወንጀል ድርጊት የተገኘ ንብረትን ሕጋዊ ማስመሰልና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን ረቂቅ አዋጅ ማጽደቁ ይታወሳል።


 

ይሁንና አዋጁ ታትሞ ከመውጣቱ በፊት የምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮችና የቋሚ ኮሚቴ አባላት አሻሚ ትርጉም ያመጣል በአተገባበር ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል ያሉትን አንድ ድንጋጌ እንዲወጣ የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል።


 

የውሳኔ ሀሳቡን ያቀረቡት በምክር ቤቱ የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ኢሳ ቦሩ፣ አዋጅ ቁጥር 780/2005ን ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁጥር 1387/2017 ላይ ከነባሩ አዋጅ አንቀፅ 26 ንዑስ አንቀፅ (3) ቀጥሎ አዲስ ንዑስ አንቀፅ (4) ማሻሻያ የተደረገበት መሆኑን አብራርተዋል።

ድንጋጌው በአተገባበር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር ስለሚችል ድንጋጌውን ማውጣት ማስፈለጉ ተገልጿል።

የምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፣ የሚወጡ አዋጆች አተገባበር ላይ ክፍተት እንዳይፈጥሩ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ነው የገለጹት።

በዚህ ረገድ ምክር ቤቱ ውሳኔ የሰጠበትን አዋጅ በድጋሚ አይቶ እንዲታረም ማድረጉ ተገቢና ትክክለኛ ውሳኔ ነው ብለዋል።

የሚጸድቁ አዋጆች ላይ የሚታዩ ክፍተቶች ከየትኛውም ወገን ቢነሱ የተነሳው ሀሳብ ተገቢነት ታይቶ እንዲታረም የሚደረግ መሆኑንም ነው ያስረዱት።

የምክር ቤቱ አባላትም አዋጁ ወደ ህትመት ከመሄዱ በፊት መታረሙ ተገቢ መሆኑን ደግፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም