የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በመላው ሀገሪቱ መድረስ የሚያስችል አቅም ፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በመላው ሀገሪቱ መድረስ የሚያስችል አቅም መገንባት መቻሉን የማህበሩ ፕሬዚዳንት አበራ ቶላ አስታወቁ።

ማህበሩ "90 ዓመታትን የተሻገረ የሰብዓዊ አገልግሎት አሻራ” በሚል መሪ ሃሳብ ነገ የማጠቃለያ መርሃ ግብር ያካሂዳል።

አቶ አበራ ቶላ የማህበሩን 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ምክንያት በማድረግ በሰጡት መግለጫ፤ ማህበሩ የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ ችግሮች በተከሰቱባቸው አካባቢዎች የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ ከማድረስ በተጨማሪ ተቋማትን የማቋቋም ስራ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ማህበሩ በኢትዮጵያ የደም ባንክ በማቋቋም እና ለተጎጂዎች የአንቡላንስ አገልግሎት ያስጀመረ ተቋም እንደሆነም ተናግረዋል።

ባለፉት 90 ዓመታት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በርካታ ሰብዓዊ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተው፤ በዚህም ማህበሩ ችግር ባጋጠመበት ቦታ በ72 ሰዓታት ውስጥ መድረስ የሚያስችል አቅም መገንባቱን አክለዋል።

የወጣቶችን ሰብዕና መቅረፅና የማህበረሰቡ እሴቶች እንዲከበሩ ማድረግ የሚያስችል የሰብዓዊነት ትምህርት ቤት በማቋቋም ትምህርት መስጠት መጀመሩን አስታውቀዋል።

በመድረኩ ማህበሩን ሲደግፉ የነበሩ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚመሰገኑበት ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግ ሂደት ውስጥ ህይወታቸውን ያጡ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ዜጎች እንደሚዘከሩም ተናግረዋል።


 

የማህበሩ ዋና ፀሃፊ አበራ ሉሌሳ በበኩላቸው፤ ማህበሩ በራሱ አቅም ለመተዳደር የተለያዩ ሃብት የማመንጨት ስራዎች እየሰራ እንደሚገኝ አክለዋል።

የማህበሩ አጠቃላይ ካፒታል ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን ጠቅሰው፤ ከበጎ ፈቃደኞች የሚደረገው ድጋፍ፣ የገቢ ማሳደጊያ እና የማስፋፍያ ስራዎች በተሻለ ሁኔታ እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

ለስድስት ወራት በክልሎች እና ዞኖች በተለያዩ መርሃ ግብሮች ሲከበር የቆየውን 90ኛ ዓመት በዓል ነገ እንደሚያጠቃልል ገልጸዋል።

በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል በሚከናወነው መርሀግብር የማህበሩን የ90 ዓመታት ጉዞ የሚያሳይ ኢግዚቢሽን እንደሚከፈትም ተናግረዋል።

ማህበሩ በቀጣይ አስር ዓመታት በራሱ ገቢ ለመንቀሳቀስ ከተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑ ተገልጿል።

ማህበሩ በተለያዩ ቦታዎች ያሉትን ህንፃዎች በማከራየት ገቢ በማመንጨት፣ ባለው የእርሻ መሬቶች ላይ የማምረት፣ የአባላትን ቁጥር በማሳደግ ከውጭ የሚያገኘውን እርዳታ ለመቀነስ እየሰራ መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም