የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በበጀት ዓመቱ በእቅድ የያዛቸውን ተግባራት ለማሳካት ያደረገው ርብርብ ውጤታማ ነው - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በበጀት ዓመቱ በእቅድ የያዛቸውን ተግባራት ለማሳካት ያደረገው ርብርብ ውጤታማ ነው - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2017 (ኢዜአ)፦የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2017 በጀት ዓመት በእቅድ የያዛቸውን ተግባራት ለማሳካት ያደረገው ርብርብ ውጤታማ እንደነበር አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
ምክር ቤቱ ባካሄደው 3ኛ ልዩ ስብሰባ ላይ የበጀት ዓመቱ የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በወቅቱ ምክር ቤቱ የሚያወጣቸው አዋጆች በአግባቡ ተፈፃሚ እንዲሆኑ ከመፅደቃቸው በፊት ተገቢው ምርመራ እንደሚደረግባቸው አንስተዋል።
ሕጎች ከፀደቁ በኋላም በአግባቡ መፈፀማቸውን ኦዲት ማድረግ መጀመሩን አስታውቀዋል።
የምክር ቤቱ የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎችም በተቀመጡ አቅጣጫዎች መሰረት እየተመሩና የተጠያቂነት አሰራርም ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ምክር ቤቱ በበጀት ዓመቱ በእቅድ የያዛቸውን ተግባራት ለማሳካት ያደረገው ርብርብ ውጤታማ እንደነበር ነው የገለጹት።
በቀጣይ በምክር ቤቱ አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን የነበሩ ጥንካሬዎችን በማስቀጠል ያጋጠሙ ክፍተቶችን በመሙላት የተሻለ ሥራ ለመከወን ሁሉም አባላት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አንስተዋል።
ሪፖርቱን ያቀረቡት የምክር ቤቱ ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ ምክር ቤቱ ባሉት አደረጃጀቶች በእቅድ የያዛቸውን ሥራዎች በብቃት ለመፈፀም በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
በተለይ ምክር ቤቱ በሕግ የተሰጠውን አራት ዋና ዋና ተልዕኮዎች ለማሳካት የሰራቸው ሥራዎች ውጤታማ ናቸው ብለዋል።
ሕጎች ከመፅደቃቸው በፊትም በየደረጃው ያሉ የምክር ቤቱ የሕግ ክፍል ባለሙያዎችና የቋሚ ኮሚቴ አባላት ዝርዝር ምርመራ እንደሚያደርጉበት ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈ የአስረጂና የሕዝብ ውይይት መድረኮችን በማመቻቸት በህጎቹ ላይ ግልፅነት እንዲፈጠር ተደርጓል ነው ያሉት።
በበጀት ዓመቱ ምክር ቤቱ ባካሄዳቸው 43 መደበኛ እና ልዩ ስብሰባዎች ከ50 በላይ አዋጆችን መርምሮ ማፅደቁን ነው የገለፁት።
ምክር ቤቱ በ2017 በጀት ዓመት ለሀገርና ሕዝብ ሁለንተናዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ሕጎች መርምሮ ማፅደቁንም አብራርተዋል።
በፓርላማ ዲፕሎማሲ ሥራም ከተለያዩ አገራት የፓርላማ ልዑክ ቡድን ጋር አገራዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የዲፕሎማሲ ግንኙነትን የሚያጠናክሩ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።
ምክር ቤቱ ባሉት 13 ቋሚ ኮሚቴዎች በአስፈፃሚ አካላት እቅድ ላይ ክትትልና ድጋፍ ማድረጉንም ነው በሪፖርቱ ያብራሩት።
የምክር ቤቱ አባላት በዓመት ሁለት ጊዜ የሚያካሂዷቸው የምርጫ ክልል የውክልና ሥራም በአግባቡ እየተመራና ሕዝቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎችም ደረጃ በደረጃ ምላሽ እያገኙ መሆናቸውን አንስተዋል።