የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ሥርዓት ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት ገንቢ ሚናችንን እንወጣለን - ኢዜማ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ዴሞክራሲ ሥርዓት ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት ገንቢ ሚናውን እንደሚወጣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) ፓርቲ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) ፓርቲ "በሀሳብ እንፎካከራለን፤ ስለሀገር እንተባበራለን" በሚል መሪ ሀሳብ ያካሄደው 2ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ተጠናቋል።

ከሰኔ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት በተካሄደው የፓርቲውን ሁለተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ሲያጠናቅቅም የፓርቲውን ሊቀ-መንበር እና ምክትል ሊቀ-መንበር መርጧል።

በዚህም መሰረት ሙሉዓለም ተገኘወርቅ(ዶ/ር) ሊቀመንበር፣ አቶ ማዕረጉ ግርማ ምክትል ሊቀ መንበር እንዲሁም አቶ ዋሲሁን ተስፋዬን የፓርቲው ዋና ጸኃፊ በማድረግ ሰይሟል።

በተጨማሪም የፋይናንስና ትሬዠሪ፣ የሕገ-ደምብና ትርጉም እንዲሁም የኦዲት እና ኢንስፔክሽን ኃላፊዎችን መርጧል።

በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) ምክትል መሪ አርኪቴክት ዮኃንስ መኮንን÷ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ባህል ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር ፓርቲያቸው በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በዳበረ የዴሞክራሲ ባህል የተሻለና ሰላማዊ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲኖራት ለማስቻል በሚደረገው ጥረት ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲ ድርጅቶች ጋር በትብብር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

በቀጣይም ጠንካራ ተፎካካሪና አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲ ሆኖ ለመቅረብ ተመሳሳይ ፍላጎት ካላቸው ሌሎች ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑንም አንስተዋል።

ለዚህም የፓርቲው አመራርና አባላት ፍጹም ሰላማዊ የፖለቲካ አካሄድን በመከተል ለተሻለ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ አብራርተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲ የሪዮተ-ዓለማዊ ሃሳብ ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ የጋራ በሚያደርጉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞችና ፍላጎቶች ላይ በትብብር መስራት እንደሚያስፍልግም አስገንዝበዋል።

በፓርቲው 2ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት በማስቀደም ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በጥልቀት መምከሩን ተናግረዋል።

የፓርቲው ሊቀመንበር፣ ምክትል ሊቀ መንበር፣ ዋና ጸኃፊ፣ የፋይናንስና ትሬዠሪ፣ የሕገ-ደምብና ትርጉም እንዲሁም የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኃላፊዎች ምርጫ ሂደትም የውስጠ ዴሞክራሲ ባህል ግንባታን ባሳየ መልኩ መከናወኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) በሊቀ-መንበርነት የተመረጡት ሙሉዓለም ተገኘወርቅ(ዶ/ር)÷ ለተሻለ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባህል ግንባታ የበኩላቸውን ገንቢ ሚና በመወጣት የተጣለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም