ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እርስ በእርስ የተሳሰረና የዳበረ አሰባሳቢ ትርክት ለማስረጽ የጎላ ሚና እንዳለው ተመላከተ - ኢዜአ አማርኛ
ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እርስ በእርስ የተሳሰረና የዳበረ አሰባሳቢ ትርክት ለማስረጽ የጎላ ሚና እንዳለው ተመላከተ

ሀዋሳ፤ ሰኔ 29/2017(ኢዜአ)፦ ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የእርስ በእርስ ትስስርንና ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር እንዲሁም የዳበረ አሰባሳቢ ትርክት ለማስረጽ የጎላ ሚና እንዳለው ተመላክቷል።
የ2017 ዓ/ም ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች ሀዋሳ ከተማ የገቡ ሲሆን የተለያዩ በጎ ተግባራትን እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡
በአቀባበል ሥነ-ሥርዓቱ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት በብልፅግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና ርዕዮተ ዓለም ዘርፍ ኃላፊ አስፋው ጎኔሳ አገልግሎቱ የእርስ በእርስ ትስስርን ለማጠናከር ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
ይህም እርስ በእርስ የተሳሰረና የዳበረ አሰባሳቢ ትርክት እንዲሰርፅ የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል ፡፡
ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችም ከሰብዓዊ ተግባራቶቻቸው ጎን ለጎን የየአካባቢውን ባህል፣ ቋንቋና ሌሎች መገለጫዎች በውል እንዲገነዘቡና የጋራ መልካም እሴቶችን እንዲያዳብሩ ዕድልን የሚሰጥ ኩነት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
የሲዳማ ክልል ሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ እመቤት ኢሳያስ፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ወጣቱ ትውልድ ሀገሩን ለመገንባት የሚያስችለውን አንድነት እንዲፈጥር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
ወጣቶቹ በሀዋሳ ቆይታቸው በየአካባቢያቸው ያለውን መልካም እሴት ለሌሎች የማስተዋወቅ፤ እነርሱም የሲዳማን የአብሮነትና የሠላም እሴት በሚገባ ተረድተው የሚመለሱበት አጋጣሚን እንደሚፈጥርም አመልክተዋል፡፡
ወጣቶቹ በቆይታቸው የፅዳት፣ የደም ልገሳ፣ አረጋውያንን የመንከባከብ፣ ህሙማንን የመጠየቅና ሌሎች በጎ ተግባራትን እንደሚከናውኑም ጠቁመዋል፡፡
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች በጎ-ፈቃድ አገልግሎት ዴስክ ባለሙያ የሆኑትና የቡድኑ አስተባባሪ እንደገና ፍቃዱ ይህ ኩነት እንደ ሀገር ለአራተኛ ጊዜ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በአጠቃላይ ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ 102 የሚሆኑ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በሁለት ቡድን ተከፍለው ወደተለያዩ አካባቢዎች በመሄድ አገልግሎቱን እየሰጡ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡
ከበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መካከል ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመጣው ወጣት ደሳለኝ ማሞ እንደገለፀው፤ በጉዟቸው የተለያየ ባህልና እሴት እንዲሁም የአኗኗር ዘይቤ እንዲገነዘቡ ዕድል መፍጠሩን ገልጿል፡፡
በሀዋሳ ከተማ ተገኝቶ ደም መለገስ መቻሉ ልዩ ስሜት እንዳሳደረበት የገለፀው ወጣቱ ደም በመለገስ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት በመታደጌ ትልቅ ደስታ ይሰማኛል ብሏል፡፡
የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ዛሬ ጠዋት በሀዋሳ ከተማ ፍቅር ሀይቅ ዳርቻ የጽዳት ስራ ያከናወኑ ሲሆን በቀጣይም የተለያዩ የበጎ ፈቃድ ተግባራትን ያከናውናሉ፡፡