በኮሞሮስ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል - ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀስላሴ - ኢዜአ አማርኛ
በኮሞሮስ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል - ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀስላሴ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2017(ኢዜአ)፦ በኮሞሮስ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይሰራል ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀስላሴ ገለጹ።
ኮሞሮስ ነፃነቷን የተጎናጸፈችበትን 50ኛ ዓመት የነፃነት በዓል የተለያዩ ሀገራት መሪዎች እና በሺዎች የሚቆጠሩ የሀገሪቱ ዜጎች በተገኙበት በድምቀት አክብራለች።
በክብረ በዓሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀስላሴ፣ የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሀሰን፣ የሞሪታንያ ፕሬዚዳንት ሞሀመድ ኡልድ ጋዙዋኒ እንዲሁም የሴኔጋል፣ የማዳጋስካር፣ የሞሮኮ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ፣ የፈረንሳይና የሌሎች ሀገራት ተወካዮች ተገኝተዋል።
በዓሉን የታደሙት ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀስላሴ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ በኢትዮጵያ እና በኮሞሮስ መካከል ያለው ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይሰራል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በኮሞሮስ የነፃነት በዓል መሳተፏ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት እያደገ መምጣቱን ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን የቆየ ወዳጅነት በማጠናከር አህጉራዊ ትስስርና አንድነት እንዲጎለብት እንደምትሰራ ተናግረዋል።
በበዓሉ ላይ የኮሞሮስ ፕሬዚዳንት አዛሊ አሱማኒ ባስተላለፉት መልዕክት በፀረ ቅኝ ግዛት ትግል ሂደት መስዋዕትነት ለከፈሉ ጀግኖች ክብር ይገባቸዋል ብለዋል።
ከነፃነት በኃላ ባለፋት 50 ዓመታት የተገኙ ለውጦች ሀገሪቱን ወደ ተሻለ የታሪክ ምዕራፍ እንዳሸጋገራት መናገራቸውን ኢዜአ ከስፍራው ዘግቧል።
በትምህርት፣ በጤና፣ በገቢ፣ በቱሪዝም እና በመሰረተ ልማት ዘርፎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እንደተመዘገቡም ነው ፕሬዚዳንቱ የገለጹት።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2023/2024 ለ1 ዓመት ያክል የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር በመሆን ያገለገሉት ፕሬዚዳንቱ ኮሞሮስ ባለፋት ጥቂት አመታት ለአፍሪካ ሰላም፣ ፀጥታና አንድነት መረጋገጥ የበኩሏን ድርሻ እየተወጣች ነው ብለዋል።
አሁን ጊዜው የተሻለ የፖለቲካ መረጋጋት የተገኘበት በመሆኑ ህዝቡ ትኩረቱን ወደ ልማት ማድረግ እንደሚገባውም ነው ያስገነዘቡት።
በተለይ ወጣቱ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚው በመግባት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ዘመናዊ፣ አስተማማኝና የላቀ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል።
ኮሞሮስ ቀላል የማይባል ገቢ ከዳያስፖራው እንደምታገኝ ፕሬዚዳንቱ ጠቁመው ዳያስፖራዎች በሀገሪቱ የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በሀገራቸው ኢንቨስት በማድረግ የወቅቱ የኮሞሮስ ጥያቄ የሆነውን ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲያፋጥኑም ጠይቀዋል።
ኮሞሮስ ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ነፃ የወጣችው በኢትዮጵያ አቆጣጠር ሰኔ 29/1967 ዓ.ም ነው።