ሆስፒታሉ የህክምና አሰጣጡን በዘመናዊ መሳሪያ በማደራጀት የአገልግሎት ጥራት የሚያስጠብቁ ተግባራት እያከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሆስፒታሉ የህክምና አሰጣጡን በዘመናዊ መሳሪያ በማደራጀት የአገልግሎት ጥራት የሚያስጠብቁ ተግባራት እያከናወነ ነው

ወልዲያ፤ ሰኔ 29/2017 (ኢዜአ)፡- የወልዲያ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የህክምና አሰጣጡን በዘመናዊ መሳሪያ በማደራጀት የአገልግሎት ጥራት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።
ሆስፒታሉ 80 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው የሲቲ ስካን ማሽን ከክልሉ ጤና ቢሮ በድጋፍ አግኝቷል።
የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ፍስሃ የኋላው ለኢዜአ እንደገለጹት ሆስፒታሉ የቀዶ ጥገና፣ የላብራቶሪ፣ የራጅና ሌሎች የህክምና አገልግሎቶችን በዘመናዊ መሳሪያ በማደራጀት የተሻለ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
በሆስፒታሉ በዚህ አመት የኦክስጅን ማምረቻ ተቋቁሞ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም ጠቅስዋል።
በዛሬው እለትም ከክልሉ ጤና ቢሮ 80 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የሲቲ ስካን ማሽን የተበረከተለት መሆኑን ጠቁመው ማሽኑ እስከ ከሐምሌ 2017 ዓ.ም መጨረሻ ተከላው ተጠናቆ ስራ እንደሚጀምር አመላክተዋል ።
ሆስፒታሉ ለከፍተኛ ህክምና ሪፈር ከሚልካቸው ህሙማን ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑት የሲቲ ስካን መሳሪያ አገልግሎት የሚፈልጉ መሆናቸውን ጠቁመው የመሳሪያው መገኘት ህሙማንን ከእንግልት የሚታደግ ጭምር መሆኑን አስታውቀዋል ።
የወልዲያ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባና የሆስፒታሉ የቦርድ ስብሳቢ አቶ ዱባለ አብራሬ በበኩላቸው ሆስፒታሉ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጥ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል ።
ዛሬ ከክልሉ ጤና ቢሮ የተገኘው የሲቲ ስካን ማሽንም የጥረቱ አካል መሆኑን አስታውቀዋል ።