በሶማሌ ክልል የመምህራንን እጥረት ለመቅረፍ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው

ጅግጅጋ፤ ሰኔ 29/2017(ኢዜአ)፦ በሶማሌ ክልል የመምህራንን እጥረት ለመቅረፍ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የዶክተር አብዱልመጂድ ሁሴን የመምህራን ኮሌጅ ለ31ኛ ጊዜ ያስተማራቸውን 230 መምህራንን ለመጀመሪያ ጊዜ በመጀመሪያ ዲግሪ ዛሬ ያስመረቀ ሲሆን ከተመራቂዎቹ መካከል 13ቱ ሴቶች መሆናቸው ተገልጿል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት የሶማሌ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ መሐመድ ሼክ ዓደን፣ ምሩቃን በቀሰሙት ዕውቀት ህዝባቸውን ለማገልገል መትጋት አለባቸው ብለዋል።

ከክልሉ ስፋት አንጻር አሁንም ከፍተኛ የመምህራን እጥረት ያለ ሲሆን የዛሬ ተመራቂዎች ከዚህ አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።


 

የክልሉ ትምህርት ቢሮ የተሻለ ትውልድ ማፍራት ይቻል ዘንድ የመምህራን እጥረትን ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑንና በክልሉ ከሚገኙ ሶስት መምህራን ኮሌጆች ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን የትምህርት ጥራትን ማሻሻል የሚያስችሉ አስፈላጊ ግብዓቶችን የማሟላት ተግባር በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የዶክተር አብዱልመጂድ ሁሴን የመምህራን ኮሌጅ ዲን መሀመድ ዓሊ አያንሌ በበኩላቸው ኮሌጁ የክልሉን ሁለንተናዊ ዕድገትና የለውጥ ጉዞ ለማፋጠን አስተዋጽኦ የሚያበረከቱ መምህራንን እያፈራ ይገኛል ብለዋል።

ኮሌጁ ከዚህ ቀደም መምህራንን በሰርተፊኬትና በዲፕሎማ ሲያሰለጥን እንደቆየ ጠቅሰው ዛሬ ደግሞ ለመጀመሪያ በዲግሪ ደረጃ ያሰለጠናቸውን መምህራን ማስመረቁን ገልፀዋል።

ተመራቂዎቹ በቀሰሙት ዕውቀት በመታገዝ ህዝብና ሀገርን በቁርጠኝነት ማገልገል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም