ከኢንዱስትሪ ፓርኩ እየተገባደደ ባለው በጀት ዓመት ወደ ውጪ ከተላከ የአቮካዶ ዘይት 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ተገኝቷል

ሀዋሳ፤ ሰኔ 29/2017(ኢዜአ)፦ ከይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ እየተገባደደ ባለው በጀት ዓመት ወደ ውጪ ከተላከ የአቮካዶ ዘይት 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ መገኘቱን የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሀይሉ ዬተራ ለኢዜአ እንዳሉት ፓርኩ ባለፉት ዓመታት በግብርና ሽግግር እና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ከማሳደግ አንጻር አበረታች ስራ እየሰራ ይገኛል።


 

መንግስት ፓርኩን ለማጠናከር የሚያደርጋቸው ድጋፎች ውጤት እያመጡ መሆኑን አንስተው ከጊዜ ወደ ጊዜ የባለሀብቱ ተሳትፎም እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።

በዚህ ወቅትም ከ30 በላይ ኩባንያዎች በፓርኩ እያለሙ መሆናቸውን ገልጸው ከእነዚህም ስምንቱ አቮካዶ፣ ወተት፣ ማርና ቡና ምርቶች በማቀነባበር ለውጪ ገበያ እያቀረቡ ሲሆን ቀሪዎቹ በሂደት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት ፓርኩ ለውጪ ገበያ ካቀረበው የአቮካዶ ዘይት ከ20 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታውሰው በተመሳሳይ 15 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ተኪ ምርት ማምረት መቻሉንም አመልክተዋል።

ፓርኩ ለበርካታ ዜጎች በቀጥታ የስራ ዕድል መፍጠሩንና ከክህሎት ሽግግር አንጻርም አበረታች እንቅስቃሴዎች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

ከ137 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ጋር የገበያ ትስስር መፍጠሩንም ጨምረው ጠቁመዋል።

በቀጣይ በፓርኩ ውስጥ ስራ ለመጀመር በሂደት ላይ የሚገኙ 32 ኩባንያዎች በሙሉ አቅማቸው ስራ ሲጀምሩ ከ20 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጠርም አመልክተዋል።

እየተገባደደ ባለው በጀት ዓመት ወደ ውጪ ከተላከ የአቮካዶ ዘይት 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚጠጋ ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።


 

የሲዳማ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊና የኮርፖሬሽኑ ቦርድ ሰብሳቢ አራርሶ ገረመው(ዶ/ር) በበኩላቸው ለኢንዱስትሪ ፓርኩ የሚቀርቡ የግብርና ግብዓቶችን ማስፋትና ጥራትን ማስጠበቅ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለዚህም ከፍተኛ የምርት ሰንሰለት ባለባቸው ሰባት ወረዳዎች የሚገኙ ከ40ሺህ ለሚበልጡ አርሶ አደሮች ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኩ የአቮካዶ ዘይት በማቀነባበር ለውጪ ገበያ እያቀረበ የሚገኘው የ'ጎልደን ኦርጋኒክ አቮካዶ ኦይል' ፋብሪካ ተወካይ ሚሊዮን ቴጎ፤ በመጀመሪያ ዙር 80ሺህ ኪሎ ግራም ድፍድፍ የአቮካዶ ዘይት ለውጪ ገበያ መቅረቡን ተናግረዋል።


 

ፋብሪካው ከበርካታ የአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር የምርት ገበያ ትስስር በመፍጠር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም ከ60 በላይ ቋሚ የስራ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።

በፋብሪካው የስራ ዕድል ተጠቃሚ የሆነው ወጣት ብሩክ ባጥሶ፤ የኮሌጅ ተመራቂ ሲሆን ከአካባቢው ሳይርቅ ባገኘው የስራ ዕድል ተጠቅሞ ራሱንና ቤተሰቡን እየረዳ መሆኑን ተናግሯል።

የፋሚሊ የማር ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ ዘርይሁን ንጉሴ፣ በየካቲት ወር 2017 ዓ.ም ወደ ስራ የገባው ፋብሪካው በፓርኩና አካባቢው ያለውን ምርትና ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በማር ማቀነባበር ላይ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ማር በዓለም ደረጃ ተፈላጊ መሆኑን አንስተው ጥራት ያለውን የማር ምርት በማቀነባበር ገበያው ላይ በስፋት ለመግባት እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

በ294 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንደስትሪ ፓርክ በ2013 ዓ.ም መጋቢት ወር ላይ ወደ ስራ መግባቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም