በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ማህበረሰብን በማሳተፍ በትኩረት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ማህበረሰብን በማሳተፍ በትኩረት እየተሰራ ነው

ወላይታ ሶዶ፤ ሰኔ 29/2017(ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ማህበረሰብን በማሳተፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።
በወላይታ ሶዶ ከተማ በአንድ ባለሃብት በ60 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ የትምህርት ቤት ህንፃ ዛሬ ተመርቋል።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዱጼ ታምሩ እንዳሉት በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል።
ትምህርት ላይ መስራት ትውልድ ላይ መስራት መሆኑን ጠቁመው ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት የክልሉን ማህበረሰብ በማሳተፍ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በተለየ ትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻልና በግብዓት ማደራጀት እንዲሁም የመምህራንን አቅም ማሻሻልን ጨምሮ ለዚሁ ስራ ውጤት የሚያግዙ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውንም ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት በተቀናጀ መልኩ በተደረጉ ጥረቶች የተማሪ ውጤት እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቅሰው ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም ባለድርሻ አካል ለትምህርት ጥራት መሻሻል የሚደረገውን ጥረት ሊያጠናክር ይገባል ብለዋል።
የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፍሬው ሞገስ(ዶ/ር) በበኩላቸው ከለውጡ ወዲህ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የተጀመረው ስራ ውጤት ተመዝግቦበታል ብለዋል።
ባለሀብቶች በከተማው ያለውን የከፍተኛ ትምህርት ፍላጎት ለመሙላት የሚደረገውን ጥረት እየደገፉ መሆኑን ገልፀዋል።
የትምህርት ዘርፉን በመደገፍ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ይሰራል ያሉት ከንቲባው የባለሀብቶችን ጥያቄ በመመለስ በዘርፉ የመጣውን ለውጥ ለማስቀጠል ይሰራል ብለዋል።
ትምህርት ቤቱን ያስገነቡት አቶ ተስፋዬ ጎአ፤ 60 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ህንፃ በ2 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ማረፉን ገልፀው ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
ዘርፉን በመደገፍ በኩል የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸው ከክልል ጀምሮ እስከ ከተማ አስተዳደር ያሉ የመንግስት አካላት እየሰጡት ያለው አገልግሎት ይበል የሚያሰኝና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ነው ብለዋል።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የክልል እና የዞን አመራሮች ተገኝተዋል።