በክልሉ ግብርናን በማዘመን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የባለሃብቶች ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ

ጋምቤላ፤ ሰኔ 29/2017(ኢዜአ)፦ ‎በጋምቤላ ክልል ግብርናውን በማዘመን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የባለሃብቶች ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።

‎ርዕሰ መስተዳድሯ በጋምቤላና አበቦ ወረዳዎች ከዘርፍ አመራሮች ጋር በመሆን በባለሃብቶች የለማ የእርሻ ማሳ ዛሬ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።


 

‎ርዕሰ መስተዳድሯ በጉብኝቱ ወቅት ለኢዜአ እንደገለጹት ለአንድ ሀገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት የኢንቨስትመንት ዘርፍ ዋነኛ ድርሻ አለው።


ባለሀብቶች ባሉት ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች በመሰማራት ለክልሉ ልማትና አድገት ተሳትፏቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።


 

‎በክልሉ በተለይም የግብርናውን ልማት በማዘመን የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለተጀመረው ጥረት በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች አርሶ አደሩን በቴክኖሎጂ በመደገፍ በኩል የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸዋል።

‎በክልሉ የተፈጠረውን ሰላም በመጠቀም ባለሃብቶች በግርናው ዘርፍ እያከናወኑ ያለው ስራ በእጅጉ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው ሌሎች ባለሃብቶች ወደ ክልሉ በመምጣት በተመሳሳይ ልማት ላይ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።


 

‎የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሎው ኡቡፕ(ዶ/ር) በክልሉ አስተማማኝ ሰላም በመፈጠሩ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሰማራት ወደ አካባቢው የሚመጡ ባለሃብቶች ፍሰት እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

‎በተለይም በግብርናው ዘርፍ ፍቃድ የወሰዱ ባለሃብቶች በዘንድሮው የመኸር እርሻ ከመቸውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ ወደ ልማት በመግባት ውጤታማ ሰራዎችን እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

‎የእርሻ ማሳቸውን ካስጎበኙ ባለሃብቶች መካከል አቶ ፍቅሩ ገብረመድን በሰጡት አስተያየት በክልሉ በተለይም በግብርናው ዘርፍ መሰማራታቸውን ተናግረዋል።


 

‎የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በሁሉም ዘርፍ አስፈለጊውን ድጋፍና አገዛ እያደረገላቸው መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም