ወጣቶች አስተሳሳሪ ትርክትን በመላበስ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለሚያጠናክሩ ተግባራት ትኩረት ሊሰጡ ይገባል - አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2017(ኢዜአ)፦ ወጣቶች አስተሳሳሪ ትርክትን በመላበስ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ ይበልጥ እንዲያተኩሩ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ አስገነዘቡ።


 

”ወጣቶች በሀገርና በሀገረ-መንግሥት ግንባታ ውስጥ ያላቸው ሚና” በሚል ርዕስ በተከታታይ ሲካሄድ የቆየው ውይይት የማጠቃለያ መድረክ የሰላም ሚኒስቴር ከብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ጋር በመተባበር “ሀገሬን እገነባለሁ ኃላፊነቴንም እወጣለሁ” በሚል መሪ ሃሳብ ተካሂዷል።

አቶ አደም ፋራህ በውይይት መድረኩ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በምጣኔ ሃብት፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ እና በዲፕሎማሲ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ራዕይ አስቀምጣ እየሰራች ትገኛለች።

ይህንን ራዕይ ለማሳካት አሻጋሪ ዕሳቤዎችና የረጅም ጊዜ ዕቅድ ይዛ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሰፊ የህዝብ ቁጥር ያላት ከዚህ ውስጥም አብዛኛው ወጣት እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብቶቿ በአጭር ጊዜ ለመበልጸግ ካሏት ሰፊ እድሎችና አቅሞች መካከል መሆናቸውን አንስተዋል።

መንግስት ወጣቱን ተጠቃሚ ለማድረግና በምጣኔ ሃብት እድገት ውስጥ በማሳተፍ የወጣቱን ህልም የሚያለመልሙ እቅዶች በመተግበር ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ወጣቶች በብሔራዊና አለም አቀፍ ደረጃ ወቅቱ የሚፈልገውን የስራ ገበያ ክህሎት እንዲይዙ በኮደርስ ስልጠናና ሌሎች የትምህርትና ስልጠና ዘርፎች ኢንቨስት እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት።

ወጣቶች የግል ራዕያቸውን ከሀገር ራዕይ ጋር በማጣጣም ማዘጋጀት፣ ሀገርን በአርበኝነት ማገልገል፣ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር ለሀገራቸው ማበርከት ከሚገባቸው ቁልፍ ጉዳዮች መካከል መሆናቸውን ዘርዝረዋል።

አስተሳሳሪ ትርክትን በመላበስ የማህበረሰብን፣ የአካባቢንና የብሔርን የእርስ በእርስ ግንኙነት የሚያጠናክሩ ስራዎችን እንዲሰሩ አስገንዝበዋል።

በተመሳሳይ በጋራ ራዕይ በመመራት ለሀገርና ዘላቂ ሰላም ግንባታ ያላቸውን ቁልፍ ሚና በቁርጠኝነት እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ግጭትን የሚያባብሱ ግለሰቦችና ማህበራዊ ሚዲያ የጥላቻና ሃሰተኛ ንግግሮችን በምክንያታዊነት በመጠየቅ ለዘላቂ ሰላም የበኩሉን እንዲወጣም በአጽንኦት አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ያላትን የመበልጸግ ዕድልን እውን ለማድረግ ወጣቱ ያለውን ጉልህ ድርሻ በመረዳት ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።


 

የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ በበኩላቸው፤ ወጣቶች ኢትዮጵያ በተለያየ ወቅት የገጠሟትን ፈተናዎች ለማሻገር የተጫወቱት ሚና ጉልህ መሆኑን አንስተዋል።

በቀጣይም በማህበራዊ ትስስርና ሀገራዊ አንድነት ያላቸውን ቁልፍ ሚና በመገንዘብ ልዩነቶች በሰለጠነ መንገድ በውይይት እንዲፈቱ ሚናቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል ነው ያሉት።

የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ፕሬዝዳንት አክሊሉ ታደሰ የተካሔዱ ውይይቶች በፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብትና ማህበራዊ ዘርፎች የወጣቱን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ እንዲሁም በሚስተዋሉ ክፍተቶች ላይ ሰፊ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።


 

በተመሳሳይ በዘላቂ ሰላም ግንባታ ጥልቅ ውይይት የተደረገበትና ቀጣይ የትኩረት መስኮች ላይ ከመግባባት የተደረሰበት እንደሆነም ገልጸዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ አስተያየት የሰጡ ወጣቶች በበኩላቸው፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበሩ የሚገኙ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ወጣቱን በዘላቂነት ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆናቸውን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም