ሙስናና ብልሹ አሰራርን በመከላከል ረገድ ሚናችንን ልናጠናክር ይገባል -ቋሚ ኮሚቴው

አዳማ፤ሰኔ 29/2017(ኢዜአ)፡- ሙስናና ብልሹ አሰራርን በመከላከል ረገድ በህዝቡ የተሰጠንን ኃላፊነት በመጠቀም ሚናችንን ልናጠናክር ይገባል ሲሉ በጨፌ ኦሮሚያ የአስተዳደር፣ ህግና ሰው ሀብት ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ገብሬ ዑርጌሶ ገለፁ።

የጨፌ ኦሮሚያ ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች የተሳተፉበት በሙስና መከላከል ሂደት ላይ ያተኮረ ግንዛቤ ማሳደጊያ መድረክ በአዳማ ተካሄዷል።


 

በጨፌ ኦሮሚያ የአስተዳደር፣ ህግና ሰው ሀብት ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ገብሬ ዑርጌሶ በወቅቱ እንዳሉት ኮሚሽኑ የሙስና መከላከል ስራውን እንዲያሳካ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶ የክትትልና ቁጥጥር ስራ እየተከናወነ ይገኛል።

በህብረተሰቡ ዘንድም በሙስናና ብልሹ አሰራር ዙሪያ የአስተሳሰብና የባህሪ ለውጥ እንዲመጣ በስነ-ምግባርና ስብዕና ግንባታ ላይ የሚሰራው ስራ ይጠናከራል ብለዋል።

ህዝቡ የሙስናና ብልሹ አሰራሮች አስከፊነትን በመገንዘብ ሌብነትን እንዲታገል በተለይም የጨፌው የአስተዳደር፣ ህግና  ሰው ሀብት ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሚናውን የበለጠ አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም ገልጸዋል።

ሌሎችም የህዝብ ተመራጮች ሙስናን ለመከላከል የሚያግዙ አሰራሮች እንዲዘረጉ የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።


 

የኦሮሚያ ክልል ስነ-ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አብደላ ኦገቴ በበኩላቸው ሙስናን ለመከላከል ጠንካራ አሰራርና ህጎች እንዲወጡ በማድረግ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።

ኮሚሽኑ የሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀቶች፣ የኃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ህዝቡን የማስገንዘብና የማንቃት ስራ እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

በተለይ በስነ-ምግባርና ስብዕና ግንባታ ረገድ ከትምህርት ቤቶች ጀምሮ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቅሰው የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር እንዲዘረጋ ከተቋማት ጋር በቅርበት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የጨፌው ቋሚ ኮሚቴ አባላትና አመራሮች ከሚያደርጉት የክትትልና የቁጥጥር ስራዎች በሻገር በግንዛቤ ፈጠራ ስራ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም