ጽዳትን ባህል በማድረግ ምቹ እና ማራኪ የመኖሪያ አካባቢ መፍጠር የሁሉም ድርሻ መሆን አለበት - የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን

ሰመራ፤ ሰኔ 29/2017(ኢዜአ)፡- ጽዳትን ባህል በማድረግ ምቹ እና ማራኪ የመኖሪያ አካባቢ መፍጠር የሁሉም ድርሻ መሆን አለበት ሲሉ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ ተናገሩ።

ርዕሰ መስተዳደር አወል አርባ በተገኙበት "ፅዳትን ባህል እናድርግ" በሚል መሪ ሀሳብ የፅዱ ኢትዮጵያ የንቅናቄ መርሃ ግብር በሰመራ ከተማ ተካሄዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ እንዳሉት ከከተሞች መስፋፋትና ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ የአካባቢ ብክለትም እየሰፋ መጥቷል።


 

በተለይም ከፕላስቲክ ምርቶች አጠቃቀም ጉድለት የተነሳ እየደረሰ ያለው ብክለት ተፈጥሮን እየጎዳ መምጣቱንም ተናግረዋል።

በዚህም ሳቢያ በከተሞች ቆሻሻዎች እየተበራከቱ በመሆኑ ይህንን ለመከላከል በጋራ ፅዱ አካባቢን በመፍጠር ለመኖሪያ ምቹ እና ማራኪ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።


 

ፅዱ አካባቢን ለመፍጠር የጋራ ስራ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት የሰጡት ዋና ዳይሬክተሯ በተለይም የአካባቢ ጥበቃ ላይ የወጡ ህጎችን መፈፀምና ማስፈፀም ብሎም ማስገንዘብ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።

በተጀመረው ንቅናቄም 15 ሚሊዮን ሰዎችን ገፅ ለገፅ ለመድረስ እና በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ደግሞ 50 ሚሊዮን ሰዎች  ጋር ተደራሽ ለመሆን መታቀዱን ተናግረዋል።


 

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ በበኩላቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመረው የ"ፅዱ ኢትዮጵያ" ንቅናቄን ከግብ ለማድረስ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

ንቅናቄው በክልሉ የተጀመሩ የአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ስራዎች እንዲጎለብቱና ውጤት እንዲኖራቸው ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል።

መርሃ ግብሩ እንዲሳካም የክልሉ መንግስት ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደሚያደርግም አስረድተዋል።


 

የክልሉ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አደን ሀመና፣ የፅዱ ኢትዮጵያ መርሃ ግብርን አውን ለማድረግ የግንዛቤ ማሳደግ ስራዎች ለተከታታይ ስድስት ወራት በትኩረት እንደሚከናወኑ አስረድተዋል።

በንቅናቄ መርሃ ግብሩ ላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም